ጅማ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መርሐ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 973 ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተማሪዎቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኃላፊዋ በመልዕክታቸው፣ “ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው ኢትዮጵያን ለመገንባት እና ለማበልጸግ እንዲሁም ለዕድገቷ የመፍትሔ አካል መሆን እንዳለባቸው” ብለዋል።
ተማራቂዎቹ በሚሰማሩበት የሥራ መስክም የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል አና ለዜጎቿ ኑሮ ምቹ የሆነች ሀገር ለመፍጠር የሚደረገውን የኢትዮጵያ ብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ ጠንክረው እንዲሠሩ አስገንዝበዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) በበኩለቸው፣ ተመራቂዎች በተማሩበት የትምርት ዘርፍ ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ኅብረተሰባቸውን በቅንነት በማገልገል ለሀገራቸው እድገት ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የማኅበረሰብ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እያደረገ ወደ ኅብረተሰቡ እያደረሰ መሆኑን ገልጸው፣ ራስገዝ ለመሆን እያደረገ የሚገኘው ጥረትም ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በማታና በሳምንት የእረፍት ቀናት ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 973 ተማሪዎችን እያስመረቀ ሲሆን፣ ከተመራቂዎቹ መካከል 2 ሺህ 523 በመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም 450 በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸው የተከታተሉ መሆናቸው ተገልጿል።
በወሰኑ አውግቸው