የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በ76ኛ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዘንድሮው ተመራቂዎች ሀገራችን አዲሱን የትምህርት ሪፎርም ከጀመረች በኋላ የተመረቁ የመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች መሆናቸውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ።
በመሆኑም ቀኑ በኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የተበሰረበት መሆኑን ተናግረዋል።
ቻንስለሩ በመልዕክታቸው ሀገራት ከድህነት አረንቋ ወጥተው የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ ልዕልና ላይ ለመድረስ የትምህርት ዘርፍ እና ሪፎርም ወሳኝ ሚና እንዳለው በሰፊው አብራርተዋል።
ለዚህም ቻይናን በምሳሌነት ያነሱ ሲሆን፣ ሀገሪቱ በታሪኳ ከገጠማት የባህል አብዮት ምስቅልቅል ልትወጣ የቻለችው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ነፃ የሳይንስ እና ምርምር ማዕከል በማድረግ እና የትምህርት ጥራትን ከታች ጀምሮ በትኩረት በመምራቷ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ደቡብ ኮሪያ ከጦርነት ማብቂያ በኋላ በነበረባት የከፋ ድህነት እና የተፈጥሮ ሀብት እጦት ውስጥ ሆና፣ ሀገርን ለመለወጥ ብቸኛው ሀብት የሰው አእምሮ መሆኑን በመገንዘብ ያደረገችውን ጉዞ አውስተዋል።
የኮሪያ መንግሥት ከፍተኛ በጀት ወደ ትምህርት በማዞር፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ትምህርትን ከኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ሳምሰንግ እና ሃዩንዳይ ያሉ ግዙፍ ተቋማትን መፍጠር እንደቻለ ቻንስለሩ አስረድተዋል።
የዛሬዎቹ ተመራቂ ተማሪዎች ታላላቅ ሀገራት በተጓዙበት የለውጥ መንገድ ላይ በመቆም፣ ያገኙትን በቂ ዕውቀት ተጠቅመው ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በለሚ ታደሰ