የኦሮሚያ ክልል ርዕስ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የቦረና ዞን ከተረጂነት ተላቆ የብልፅግና መሰረትና የምርታማነት ማዕከል እየሆነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ለረጅም ጊዜ እንደ ዳርቻና የድንበር ጠባቂ ብቻ ይታይ የነበረውን የቦረና አርብቶ አደር ማኅበረሰብ፣ በአሁኑ ወቅት የክልሉ የለውጥ መንግሥት በወሰደው ቁርጠኝነት የምርታማነት ኃይልና የዘላቂ ብልፅግና መሠረትነት እያሸጋገረው መሆኑን አቶ ሽመልስ አስታውቀዋል።
ለዓመታት የአገሪቱ ሩቅ ዳርቻ ተደርጎ ይታይ የነበረው ቦረና ዛሬ የኦሮሚያ ስትራቴጂካዊ ትጥቅና የምርታማነት ማዕከል መሆኑን የገለጹት አቶ ሽመልስ፤ የተጀመረውን አበረታች ሽግግር ከአጭር ጊዜ ውጤት ወደ ዘላቂ የምርታማነት ሥርዓት የማሳደግ ሥራ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ይህ የሽግግር ሥራ የአርብቶ አደሩን የቆየ የአኗኗር ዘይቤ ከማዘመን ባለፈ፣ አዳዲስ ዘመናዊ የማምረቻ ዘዴዎችን እርስ በእርስ በሚደጋገፉ ሁለት ዋና ዋና መንገዶች ማስተግበር ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፤ ለአርብቶ አደሩ ዋነኛ የሕይወት መሠረት የሆኑትን የውሃና የእንስሳት መኖ አቅርቦት ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ሰፋፊ መሠረተ ልማቶች ተገንብተዋል።
ከእነዚህም መካከል፦ በ"ፊና" ፕሮጀክት አማካኝነት 23 ግድቦች የተገነቡ ሲሆን፣ በዘንድሮው ዓመት ብቻ 208 የቤተሰብና 26 የማኅበረሰብ ኩሬዎች ተቆፍረው ውሃ መያዝ ጀምረዋል።
በትልቅ በጀት እየተገነባ ያለው የቦረና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም በመቶዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ተዘርግቶ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።
በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም ትራክተሮች፣ የሳር ማጨጃና ማሰሪያ ማሽኖች ቀርበው 65 ሺህ ሄክታር መሬት በተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎች እንዲለማ ተደርጓል።
የተመረተውን መኖ በዘላቂነት ለማከማቸት 19 ታላላቅ መጋዘኖች የተገነቡ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 1.1 ሚሊዮን የሳር እሽጎችን (ቤል) የመያዝ አቅም ፈጥረዋል። በያቤሎ ከተማ የተገነባው ‘የእንስሳት ጤና ምርምር ማዕከል’ እና የተዘረጋው የገበያ ትስስርም የዘርፉን ጠቀሜታ አሳድጎታል።
አቶ ሽመልስ አክለውም፣ በመንገድ፣ በአውሮፕላን ማረፊያ፣ በሎጂስቲክስና በቱሪዝም መሠረተ ልማቶች አማካኝነት ርቆ የነበረውን ቦረናን ወደ ኦሮሚያ የትስስር ማዕከልነት በመለወጥ፣ የ"ቡዕራ ቦሩ" መሠረታዊ ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን በስፋት በማስፋፋት የማኅበረሰቡ የመቋቋም አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር መደረጉን ጠቁመዋል።
ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን የግብርና ሜካናይዜሽን ስትራቴጂን ወደ ሥራ ማስገባት ታሪካዊ ለውጥ ማምጣቱን ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በቦረና ዞኖች በአጠቃላይ ይታረስ የነበረው መሬት ከ200 ሺህ ሄክታር የማይበልጥና በ2013/14 የምርት ዘመን የስንዴ ልማት ከ7 ሺህ ሄክታር ያልበለጠ እንደነበር አስታውሰዋል።
ሆኖም መንግሥት በሰጠው ልዩ ትኩረትና በስንዴ ኢኒሼቲቭ አማካኝነት በዘንድሮው የምርት ዘመን በሁለቱ ዞኖች በአጠቃላይ ከግማሽ ሚሊዮን (500,000) ሄክታር በላይ መሬት በማረስ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እየተጠበቀ ይገኛል።
ከዚህ ውስጥ ስንዴ ብቻ በ100 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለመ ሲሆን፣ ከ2 ሚሊዮን 200 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል። ይህ ስኬት አጭሩን የዝናብ ጊዜ በቴክኖሎጂና በትራክተሮች በመጠቀም እንዲሁም ከአካባቢው ሥነ ምህዳር ጋር የሚስማማ ምርጥ ዘር በማቅረብ የተመዘገበ ታሪካዊ የእርሻ መሻሻል መሆኑ ተገልጿል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ንግግራቸውን ፤ "ዛሬ በቦረና የተዘረጋውን የስንዴ ማሳ ስንመለከት አዲስ የኢኮኖሚ ዕድልን እናያለን፤ የውሃ ግድቦችን ስንመለከት የሕይወት ዋስትናን እናያለን፤ ቦረናን ስንመለከት ደግሞ የነገዋን ኦሮሚያ የብልፅግና መሠረት እናያለን" ብለዋል።