የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ከ1.5 ሚሊየን በላይ ዜጎች የሚሳተፉበትን የክልሉን የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አስጀምረዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራውን በካፋ ዞን ጊምቦ ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማስገንባት ያስጀመሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በክልሉ 640 ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶች በማስገንባት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማኅበራዊ ተስስርን በማጎልበት እና ሀገራዊ ትስስርን በማጠናከር የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።
በዘንድሮው የክረምት ወቅት በ14 የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስኮች ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ተግባር ይከናወናልም ነው ያሉት።
በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው፣ በክልሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ላይ የሚሳተፉ ዜጎች ቁጥር በየዓመቱ እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል።
በዚሁ ሂደት የዜጎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት በየጊዜው ከፍ እያለ እንዲመጣ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሯል ብለዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የዞኑ አስተዳደር እያከናወነ ለሚገኘው ሁሉን አቀፍ ሥራ ተጨማሪ አቅም መሆኑን ገልጸው ዘንድሮውም የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችን አሟጥጦ ለመጠቀም የተቀናጀ ርብርብ እንደሚደረግ አስገንዝበዋል።
በክልሉ የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የከተማ ልማት፣ የቤቶች ግንባታ፣ የውሃ መስመር ዝርጋታና ሌሎችም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያስገኙ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተገልጿል።
በሰለሞን ባረና