አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 76ኛውን የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ በደማቅ ሁኔታ እያካሄደ ይገኛል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳስታወቁት ተቋሙ ለበርካታ ዓመታት ሲያደርገው የነበረውን የራስ ገዝነት አስተዳደር ሽግግር በተሳካ ሁኔታ አጠናቋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ ይህ ታሪካዊ የምረቃ በዓል ተቋሙ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩን በሚያከብርበት ወቅት መካሄዱ ድርብ ትርጉም እና ኃላፊነት እንደሚሰጠው ገልጸዋል።
የጀመረው የራስ ገዝነት ሥርዓትም ተቋሙ አካዳሚያዊ ፕሮግራሞቹን እንዲያስፋፋ፣ ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች በራሱ መስፈርት እንዲቀበልና አስተዳደራዊ ሥራዎቹን ይበልጥ እንዲያጠናክር ሰፊ ዕድል ይፈጥርለታል ብለዋል።
በመርሐ-ግብሩ ከተመረቁት 6 ሺህ 417 ተማሪዎች መካከል 207ቱ በሦስተኛ ዲግሪ (PhD)፣ እንዲሁም 30ዎቹ ደግሞ በሰብ-ስፔሻሊስት የሕክምና ዘርፍ የተመረቁ ናቸው።
በቅርቡ በተሰጠው ሀገራዊ የመውጫ ፈተና ዩኒቨርሲቲው ካስፈተናቸው 3 ሺህ 960 ተማሪዎች ውስጥ 91 በመቶ የሚሆኑት ማለፋቸውንና በ18 የትምህርት ፕሮግራሞች ደግሞ ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ (100%) ማለፋቸው ተገልጿል።
በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች (QS World University Rankings እና Center for University Rankings) ከአፍሪካ እና ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ መሆኑን ዶክተር ሳሙኤል ገልጸዋል።
በዓመታዊ የምርምር ሕትመት ብዛትም ከአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑት 5 ተቋማት አንዱ መሆን መቻሉን ጠቅሰዋል።
ባለፉት ሰባት አሥርት ዓመታት ከ300 ሺህ በላይ ምሩቃንን በማፍራት ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የላቀ ዐሻራ ያሳረፈው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ የራስ ገዝነት ጉዞው ቀደምት አመራሮች ባቆዩት አቅም ላይ ተመሥርቶ የላቀ ተቋም ለመፍጠር እንደሚያስችል ፕሬዚዳንቱ አጽንዖት ሰጥተዋል።
ምሩቃኑ ዓለማችን በአየር ንብረት ለውጥ እና በኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል በምትፈተንበት በዚህ ወቅት የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ጥበብ በማሳደግ እያንዳንዱን ፈተና ወደ ድል የሚቀይሩ መፍትሔ አምጪዎች እንዲሆኑ ዶ/ር ሳሙኤል አደራ ብለዋል።
በለሚ ታደሰ