የግብርና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ሀገራዊ የቡና ልማት ፓኬጅ መተግበሪያ ሰነድን ይፋ አድርገዋል።
ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚተገበረው ይህ የቡና ልማት ፓኬጅ በኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኘውን የቡና ምርት በጥራት እና በብዛት ለማሳደግ ያለመ ነው።
የቡና ምርትን ለማሳደግ አዲስ ምዕራፍ ይዞ በመጣው በዚህ የፓኬጅ ሰነድ እና ባካተታቸው ጉዳዮች ዙሪያ፣ በቡና ልማት ላይ ከተሰማሩ አርሶ አደሮች ጋር ሰፊ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
መተግበሪያ ሰነዱ ከምርት ዝግጅት ጀምሮ እስከ ገበያ ትስስር ድረስ ያሉትን ሰንሰለቶች በሙሉ የሚያጠቃልል ነው።
በተለይም የችግኝ ጣቢያ አያያዝ፣ የጥላ ዛፎች ዝግጅት፣ የቴክኒክና የኮንሰርቬሽን ሥራዎች፣ የቡና ማሳ አያያዝ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) አጠቃቀም፣ የምርት አሰባሰብ፣ የድኅረ-ምርት አያያዝ እንዲሁም የጥራት ቁጥጥር እና የገበያ ትስስር ላይ ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ ችግሮችን እንደሚፈታ ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ ከአንድ ሄክታር ከ7 እስከ 8 ኩንታል የቡና ምርት የሚሰበስብ ሲሆን፣ የዚህ ፓኬጅ ትግበራ ምርታማነትን ከ20 እስከ 21 ኩንታል ከፍ እንዲል የሚያስችል መሆኑ ታውቋል።
የዚህ የቡና ልማት ማደግ የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከማሳደግ ባለፈ፣ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር በውይይቱ ላይ ተብራርቷል።
በሐምራዊት ብርሃኑ