አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ለሚመጡ ጥፋቶች ካሳ እና ድጋፍ የምትጠይቅ ብቻ ሳትሆን መፍትሄ ሆና መቅረብ የምትችል አህጉር መሆን ይኖርባታል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
2ኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በይፋ ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በአየር ንብረት ለውጥ እየተጎዳ ያለውን ዓለም ለመታደግ ሀገራት ያላቸውን ሀብት ወደማየት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ሀገራት የያዟቸውን ሕልሞች ወደ መደገፍ መዞር አለባቸው ብለዋል።
አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በርካታ ችግሮች ደርሰውባታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ በየጉባዔው ስለደረሱ ችግሮች ከመወያየት መፍትሄ ማፈላለግ ላይ ማተኮር ይገባል፤ ለዚህም አፍሪካ የመፍትሔው አካል መሆን ይገባታል ብለዋል።
በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔዎች ላይ አፍሪካ ለጥቅሞቿ መደራደር ብቻ ሳይሆን መፍትሔዎቿን ይዛ መቅረብ አለባት፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በዋናነት ሀገራት በራስ አቅም የሚሠሯቸው ዘላቂ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ሥራዎችን መደገፍ ይገባዋል ነው ያሉት።
በዚሁ አግባብ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ተሞክሮዋን ለተቀረው ዓለም መግለጥ እንደምትፈልግ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህም 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረቧን ገልጸዋል።
2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፡ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በተመስገን ሽፈራው
#EBCdotstream #AddisAbaba #AfricaClimateSummit #ACS2 #PMAbiyAhmed #ClimateAction