Search

"የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመራር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ተምሳሌት የሚሆን ነው" - ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ

ማክሰኞ ጳጉሜን 04, 2017 47

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለዚህ ግድብ ግንባታ የሰጡት አመራር ለሀገራቸው ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ምሳሌ የሚሆን እንደሆነ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ተናገሩ። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢንጂነሪንግ አቅም ብቻ የሚታይበት ሳይሆን፤ የአፍሪካን የመቻል አቅም ያሳየ ተምሳሌት እንደሆነም ፕሬዚዳንት ሩቶ ገልጸዋል።

ግድቡ አፍሪካ አቅሟን ተጠቅማ የራሷን ብልፅግና ማረጋገጥ እና መጻኢ ዕድሏን መወሰን እንደምትችል ያሳየ መሆኑንም ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት። 

ይህን እውን ለማድረግ ግን አንደ አፍሪካ፣ እንደ ምሥራቅ አፍሪካ እና እንደ ናይል ተፋሰስ ሀገራት፥ ትብብር እጅጉን አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።

ታዳሽ የኃይል ምንጭን በመጠቀም የየሀገሮቻችንን ዕድገት እውን ለማድረግ በሚሠራው ሥራ፤ ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሠራ አረጋግጥዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ፕሮጀክት ሳይሆን፤ የፓን አፍሪካዊነት መገለጫ መሆኑን ፕሬዚዳንት ሩቶ ተናግረዋል።

ግድቡ አፍሪካውያን ብልፅግናቸውን ለማረጋገጥ ሊሠሯቸው ለሚገቡ ፕሮጀክቶች ማሳያ እንደሆነም ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት።

ዓላማው አፍሪካውያንን በኃይል ማስተሳሰር የሆነው የአፍሪካ ሕብረት መርህ ጋር የሚጣጣም እንደሆነም ጠቁመዋል።
በለሚ ታደሰ