Search

“ዛሬ እዚህ ሆነን የምናየው እውነት ከዚህ በፊት የሚሆን አይመስልም ነበር” - ፔትሮ ሳሊኒ

ማክሰኞ ጳጉሜን 04, 2017 53

የጣሊያኑ ሳሊኒ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ፔትሮ ሳሊኒ ዛሬ በተካሄደው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ሥነ-ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልእክት "ዛሬ እዚህ ሆነን የምናየው እውነት ከዚህ በፊት የሚሆን አይመስለንም ነበር፤ ይኸው ከ14 ዓመታት በኋላ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን ሆኗል" ብለዋል።

ግድቡ ዛሬ ላይ በሚፈለገው የውኃ መጠን ሞልቶ፣ ተርባይኖቹም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀምረዋል ያሉት ፔትሮ፣ “ሁሉም ነገር በትክክል እየሠራ ነው፤ ይህ እጅግ አስደናቂ ነው፤ እጅግ ደስ የሚል ነገር ነው” ሲሉም አክለዋል።

“ይህ ለእኔ እና ለኢትዮጵያ እውን የሆነ ሕልም ነው፤ ዛሬ ምን ያህል እንደኮራሁ ልነግራችሁ እወዳለሁ፤ ልቤ የኢትዮጵያውንን አንድነት እየዘመረች ነው” ሲሉም የተሰማቸውን ጥልቅ ስሜት ገልጸዋል።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ለመንግሥታቸው የደስታ መግለጫ መልዕክት መላካቸውንም ፔትሮ ሳሊኒ ገልጸዋል።

ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚመነጨው የኤሌትሪክ ኃይል ኢትዮጵያ አሁን ያላትን በሦሰት እጥፍ የሚጨምር መሆኑንም ያስታወሱት ፔትሮ ሳሊኒ ከሕዳሴ ግድብ ጋር የሚስተካከል የኒውክሌር ማበልጸጊያ ሲጨመር ደግሞ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ ወዳጅነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር እና ቀጣናዊ ልማትን ለማፋጠን ያገለግላል ብለዋል።

በዚህ ድንቅ ሥራ ከጅማሮው እስከ ፍፃሜው ሂደት አሻራቸውን ላሳረፉ ሁሉም ሠራተኞች ምስጋና አቅርበዋል።

በዚህ ግድብ ግንባታ ሥራ ላይ እየተሳተፉ በነበረ ወቅት በተለያዩ አደጋዎች ሕይወታቸውን ላጡ ሠራተኞች ክብር እንደሚሰጡ እና በኅሊና እንደሚያስቧቸው ተናግረዋል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነባራዊ ሁኔታዎችን በመጋፈጥ ዛሬ ለምናየው ፍሬ አድርሰውታል ሲሉም ፔትሮ ሳሊኒ ተናግረዋል።

“ይህ ግድብ እንዲገነባ ማንም አልፈለገም ነበር፤ ማንም የፋይናንስ ድጋፍ አላደረገለትም፤ በርካታ የፖለቲካ ችግሮችም ነበሩ፤ ቀላል ውሳኔዎች አልነበሩም ያሉት ፔትሮ፣ የኢትዮጵያን ባህሪ ግን በፈተናዎች እና በተግዳሮቶች መጠንከር ነው፤ ኢትዮጵያውያን ፈተናዎችን አይፈሩም” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

“ኢትዮጵያውያን ፅኑ ናቸው፤ ተገዳዳሪ ወይም ጠላት ሲያጋጥማቸው አቅማቸውን በእጥፍ በማባዛት ማሸነፍ ይችሉበታል” ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ለማንም አይንበረከኩም፤ ያመኑበትን እና የፈለጉትን ነገር ከማድረግም ወደ ኋላ አይመለሱም፤ ለዚያም ነው ኢትዮጵያ ሁሉንም ተቃውሞ እና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አልፈው ይህንን ፕሮጀክት ያሳኩት ብለዋል።

መጀመሪያ ተቃውሞ እና ፍራቻም ነበር፤ አሁን የሕዳሴ ግድብ ውኃን የሚይዘው ንጋት ሐይቅም ሙሉ ለሙሉ ሞልቷል ያሉት ፔትሮ ሳሊኒ፣ በፊት ሲፈራ እንደነበረው ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ምንም ስጋት አለመሆኑን አስመስክሯል ሲሉ ገልጸዋል።

ቤተሰባቸው ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው ተናግረው ከለገ ዳዲ ግድብ እስከ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመሥራት ለኢትዮጵያ የንፁህ መጠጥ ውኃ እና የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት መሳካት ሚና መወጣቸውን ጠቁመዋል።

ዛሬ በሕዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ የጋበዙት ልጃቸውም ከኢትዮጵያ ጋር መሥራት እንዲቀጥሉም ኃላፊነት ሰጥተዋቸዋል።

“ስለ ኢትዮጵያ ወርቅ አንብቤ ነበር፤ ይህ ወርቅ ግን እንደምናስበው ውዱ ብረት አይደለም፤ ይህ የኢትዮጵያ ወርቅ ውኃዋ ነው” ብለዋል ሳሊኒ ፔትሮ።

በዮናስ በድሉ

#ebc #etv #ebcdotstream #EBC #GERD #ሳሊኒ #salini