Search

ኢትዮጵያውያን ዓይናችንን ከፍታችሁልናል፤ እንደምንችልም አሳይታችሁናል - የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ

ማክሰኞ ጳጉሜን 04, 2017 88

በሕዳሴው ግድብ ምርቃት ላይ የተገኙት የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ፥ የሕዳሴ ግድብ እውን መሆን ውኃን ገድቦ ኃይል ከማመንጨት እና ከአስደናቂ የምህንድስና ውጤት በላይ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ግድቡ በማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የደኅንነት ዘርፎችም ከሚኖረው ጥቅም በላይ የሚያኮራው ኢትዮጵያዊያን ግድቡን እውን ለማድረግ የተጓዙበት መንገድ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

በታሪካቸው የሚኮሩት ኢትዮጵያዊያን፣ የምድረ ቀደምቷ ሀገር ዜጎች፥ ሁሉንም የሉዓላዊነት መደፈር

ሙከራዎች አክሽፈው በክብር ቆመዋል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሯ።

በግድቡ ጉብኝት ወቅት የታዘብኩት የዓድዋ ድል ተምሳሌት በምህንድስና ጥበብ ዳግም ተገልጦ ነውም ብለዋል።

"የእኔን አካባቢ የካሪቢያን ዜጎች ጨምሮ ብዙዎች ላያውቁት ይችላሉ ነገር ኢትዮጵያ ይህን ግድብ

ልትገነባ ስትነሳ ዓለም ፊቱን አዙሮባት የገንዘብ ድጋፍም ተነፍገው ነበር" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፥ ኢትዮጵያዊያን ግን እጃቸውን ሳይሰጡ ያላቸውን ሁሉ ሰጥተው እውን ማድረጋቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያዊያን ምንም እንኳን የሚፈጅባቸው ጊዜ ቢራዘም ከድል ወደ ኋላ እንደማይሉ ያውቁታልም ብለው፤ ከዓመታት ልፋት እና የድካም ጉዞ በኋላ በርካታ ገንዘብ ፈሰስ አድርገው ዛሬ ሕድሴን እንዳስመረቁም ተናግረዋል።

የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ እና የቀጠናው ሀገራት ብቻ የሚጠቅም አይደለም፤ ከዚህ አልፎ ግን ለመላው አፍሪካውያን እና መሰረታቸው አፍሪካ ለሆኑ ሕዝቦች ሁሉ ድል የሆነ የመቻላችን ምልክት ነውብለዋል።

ዛሬ በሀገሬ ባርቤዶስ፣ በመላው ካረቢያን ሀገራት፣ በአፍሪካ ስድስቱ ቀጠናዎች እና በዳይስፖራው ስም እዚህ ቆሜ ኢትዮጵያውያን ዓይናችንን ከፍታችሁለናል፤ እንደምንችልም አሳይታችሁናል ለማለት እፈልጋለው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሯ።

ዓድዋ አንድ ብንሆን ባለድል እንደምንሆን፤ ሁሉም ነገር እንደሚቻል አሳይቶናል፥ ዛሬ ደግሞ በዚህ ግድብ አብረን ስንሰራ ውጤታማ እንደምንሆን ዳግም ተመልክተናልም ብለዋል።

በሰለሞን ከበደ