የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዳሴ ግድብ ምረቃን አስመልክቶ ለኢቢሲ በላከው መግለጫ፥ ታሪካዊ ለሆነው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የምርቃት ቀን እንኳን አደረሣችሁ ሲል የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፏል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የ"አይቻልም፣ አይደፈርም" አመለካከትን የሰበረ፤ የኢትዮጵያውንን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አቅም ያሳየ፣ በሀገሪቱ አዲስ ምዕራፍ ሆኖ በኢትዮጵያውያን ደምና ላብ የተፃፈ ደማቅ ታሪክ ነው ብሏል።
በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ተጀምሮ የተጠናቀቀው ግድቡ በዓርበኞች ልጆቿ ህያው መሆን የቻለ፣ የዘመናት ቁጭትን ያስቀረ፣ ከድህነትና አለመቻል ዕሳቤ የሚያወጣ ታላቅ የታሪክ እጥፋት መሆኑንም መግለጫው አመላክቷል።
ግድቡ የብሔር፣ ፆታ፣ ዕድሜ፣ ሐይማኖት፣ ማንነት፣ የፖለቲካ አቋምና ሌሎች ልዩነቶችን ወደ ጎን አስትቶ መላ ኢትዮጵያውያንን አንድ ያደረገ መሆኑን የጠቀሰው ያወሳው፤ ለስኬቱም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን የገንዘብ፣ የዕውቀት፣ የጉልበት፣ የሞራልና የደም ዋጋ መክፈላቸውን አንስቷል።
የግድቡ ግንባታ እንዲሳካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎችና አባላት፣ ተጠሪ ተቋማትና የጽ/ቤቱ ሠራተኞችን በማስተባበር በቦንድ ግዢ፣ በክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በተለያዩ ተግባራት በመሳተፍ ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን ጠቅሷል።
#Ethiopia #GERD #Inauguration