የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼይኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ለምረቃ መብቃቱን አስመልክተው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ፕሬዚዳንቱ የግድቡ ተገንብቶ መጠናቀቅ እና ለዛሬ ምርቃት መብቃት የሀገራችን ዳግም ውልደት ተደርጎ የሚቆጠር ነው ብለዋል።
በድህነት፣ በችግር ስሟ ሲነሳ ለነበረች ሀገራችን ያንሰራራች፣ ያደገች ተብላ ለመጠቀሷ ወሳኝ መሰረት የሚጥል፣ ተወዳዳሪ ለመሆንም ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በስልጣኔ፣ በህዝብ ብዛት፣ በመልማት ተስፋዋና በእምቅ አቅሟ ከማንም አታንስም ያሉት ሼይኽ ሀጂ ኢብራሂም፤ በአሏህ ፈቃድ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ባልደረቦቻቸው ቆራጥ መሪነት፣ በልማት አርበኞቻችን ትጋት እና በህዝባችን የጋራ ትብብር ግድቡ እውን ሆኗል፤ ይህም በእጅጉ ያስደስታል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ የእኔ ነው ብለን በመረባረባችን ድሉ ተገኝቷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ እንደ ህዝብ ፍቅራችን፣ ኃይላችንን እና ህብረታችንን እንዲሁም ያሰብነውን ማሳካት እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን አንስተዋል።
በግድቡ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሰማናቸው ብስራቶችም ነገአችንን በልዩ ተስፋ እንድንጠባበቅ እና ከተባበርን ከዚህም በላይ ማሳካት እንደምንችል ያሳዩን ናቸው ብለዋል።
ምኞትና ሕልማችን እውን የሆነበትን አስደናቂ ታሪክ በዓይናቸው ለመመልከት መቻላቸው ትልቅ ደስታ እንደፈጠረባቸው የገለፁት ሼይኽ ሀጂ ኢብራሂም፤ "መላ ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን ደስ አለን" ሲሉ ነው ደስታቸውን የገለፁት።
በሀብታሙ ተክለስላሴ
#Ethiopia #GERD #Inauguration