Search

ሕዳሴ ግድብ አፍሪካ ሀብቷን በመጠቀም መፃኢ ዕድሏን በራሷ መበየን እንደምትችል ማረጋገጫ ነው"፡- ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ

ማክሰኞ ጳጉሜን 04, 2017 40

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አፍሪካ ሀብቷን በመጠቀም መፃኢ ዕድሏን በራሷ መበየን እንደምትችል ማረጋገጫ ነው ሲሉ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ያለምንም የውጭ ብድርና እርዳታ በራሷ አቅም የገነባችው የአፍሪካ ትልቁ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በራስ አቅም ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ለአፍሪካውያን ጥሩ ማሳያ ስለመሆኑ ፕሬዚዳንት ሩቶ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሑፍ ገልጸዋል።

የሕዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ ኬንያ ከኢትዮጵያ ተጨማሪ ኃይል ለመግዛት ዝግጁ መሆኗን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህም ለኬንያ አምራች፣ አግሮፕሮሰሲንግ እና አይሲቲ ዘርፎች በቂ ኃይል በማቅረብ የሥራ ዕድል ፈጠራን እና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ አጋዥ ይሆናል ብለዋል።

ማንኛውም ሀገር ሕዳሴ ግድብን መሰል የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት አጋዥ የሆኑ ፕሮጀክቶችን እንዳይገነባ ሊከለከል አይገባም፤ ምክንያቱም መሰል ፕሮጀክቶች ለአንድ ሀገር ብቻ ሳይሆን በሂደት የጋራ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ጠቃሚ ናቸውና ብለዋል።

ኢትዮያጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳንን ጨምሮ ሁሉም የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን የውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ኬንያ እንደምትደግፍ ገልጸው፤ በተለይ በስም የተጠቀሱት ሶስቱ ሀገራት በቅን ልቦና ያቋረጡትን የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በሀገራቱ መካከል የሚደረግ ምክክር ልዩነትን በድርድር በማጥበብ ፍትሃዊ ስምምነት ለመድረስ ብሎም ቀጣናዊ መረጋጋትን እና የጋራ ብልፅግናን ለማስፈን ትክክለኛው መንገድ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ በማህበራዊ ገፃቸው አስታውቀዋል።

በላሉ ኢታላ

#Ethiopia #GERD #Inauguration