Search

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የአዲስ ዓመት መልዕክት አስተላልፈዋል

ረቡዕ ጳጉሜን 05, 2017 347

 

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ 2018 , የዘመን መለወጫ በዓልን መግባት አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ ቃለ ምእዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል

በመልዕክታቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ርዕሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰንመቱ ዓመተ ምሕረት፤

በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሐዱ ኣምላክ ኣሜን!

 

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣

ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣

የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣

በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣

እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያት በሙሉ፤ 

አምላክነቱን አውቀን እንድናመልከው ዕድሜን እና ዘመናትን የሚሰጠን እግዚብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ስምንት ዓመተ ምህረት የርእሰ ዐውደ ዓመት በዓል ኣደረሰን አደረሳችሁ!

‹‹ወገብረ ኵሎ ኅቡረ ወኵሎ አሕዛበ እምአሐዱ ዕጓለ እመሕያው ከመ ይንበሩ ዲበ ኵሉ ገጸ ምድር፤ ወሠርዐ ዕድሜሁ ወዓመታቲሁ መጠነ ይነብሩ በዘየኃሥዎ ለእግዚአብሔር፤ እመ ይረክብዎ፤ ወያደምዕዎ፤ ወኢኮነ ርሑቀ እምኵልነ፡- ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደሆነ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከኣንድ ፈጠረ፤ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ደረጃ መደባላቸው፤ ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ ኣይደለም›› (የሐ. ሥራ. ፲፯÷፳፮)

ፈጣሬ ፍጥረታት እግዚአብሔር ትዕይንተ ዓለምንና በውስጡ የሚገኙ ፍጥረታትን የፈጠረ ኣምላክ ነው፤ እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት የሚታዩና የማይታዩ ተብለው በጥቅል በቅዱስ መጽሐፍ ተገልጸዋል፤ የሰው ልጅ ከፍጥረታት መካከል ሆኖ ከኣንድ ወገን የተገኘ እንደሆነ በዚህ ጥቅስ ተጽፎኣል።

የሰው ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ የተለየ ክብርና ደረጃ እንዳለው በቅዱስ መጽሓፍ በተደጋጋሚ ተገልጾኣል፤ ልዩ የሚያደርገውም ከኣፈጣጠሩ ጀምሮ ነው።

 

ሰው ልዩ ፍጡር መሆኑን ከሚገለጽባቸው መካከል እግዚአብሔር በሦስትነቱሰውን በአርኣያችንና በኣምሳላችን እንፍጠርበሚል ልዩ ኣገላለጽ መፈጠሩ፣ ኣፈጣጠሩም በእግዚአሔር መልክና ኣምሳል መሆኑ፣ በእግዚአብሔር እፍታ ሕያው ነፍስ እንዲኖረው መደረጉ፣ በሥልጣንም የፍጥረታት ሁሉ የበላይ ሆኖ መሾሙ ከሌሎች ፍጥረታት ልዩ ያደርገዋል፡፡

ከዚህ ኣንጻር ሰው በዚህ ዓለምም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ከፍጥረታት ሁሉ በላይ ነው፤ የሁሉም ገዥ ነው፤ በተለይም በዚህ ዓለም ከሰው በላይ ሆኖ የፍጡራን ገዥ የሆነ ፍጡር እንደሌለ ሁላችንም የምናየውና የምናውቀው ነው።

በላይኛው ዓለምም ቢሆን መላእክትን ጨምሮ ሰማይ እና ምድርን ከነግሣንግሡ እየገዛ ያለው ሰው የሆነ ጌታ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረት ገዥ ነው፤ እሱ ሰብእናችንን በፍጹም ተዋሕዶ የተዋሓደ በመሆኑ ሰብእናችን በተዋሕዶተ ቃል ኣምላክ ሆኖ የፍጥረታት ሁሉ ገዥ ሆኖአልና ነው።

ቅዱስ መጽሓፍምወተኰነኑ ሎቱ መላእክት ወሥልጣናት ወኵሉ ኃይል፡- መላእክት፣ ሥልጠናትና ኃይል ሁሉ ተገዙለትበማለት ይህንን ያረጋግጣል፤ ይህ እግዚአብሔር ለኛ ለሰዎች ያጐናጸፈን ግሩምና ኣስደናቂ ጸጋ ነው፤ ለዚህም ነውወሰብእ ይከብር እምኵሉ ፍጥረት፡- ሰው ከፍጥረት ሁሉ ይከብራልተብሎ የሚዘመረው።

 

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውንና ኢትዮጵያውያት!

 እኛ ሰዎች የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ሆነን እንድንኖር በእግዚአብሔር ስንፈጠር በሕይወት እንድንኖር ነው፤ እግዚአብሔር በምድር ላይ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሰውን ከኣንድ ፈጠረ የሚለው መጽሓፍ ቅዱሳዊ ኣስተምህሮም ይህንን ያመለክታል።

ሰዎች በምድር ላይ በሕይወት እንዲኖሩ የተፈጠሩ ሆነው እያለ በሕይወት እንዳይኖሩ ማድረግ ከፈቃደ እግዚአብሔር ጋር መጋጨትን ያስከትላል፤በዘመናችን ዓለማችንን እየፈተነ ያለው ተቀዳሚ ፈተና ሰዎች በሕይወት እንዳይኖሩ የማድረግ ዝንባሌ ነው።

እንደዚህ ዓይነቱ ዝንባሌ በዓለም ባይኖር ኖሮ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቈጠሩ ድሆች ባሉበት ዓለም ለሰው ልጅ ሕይወት ማጥፊያ የሚሆን መሳሪያ ለማምረት ኁልቈ መሣፍርት የሌለው ገንዘብ ኣይወጣም ነበር።

ይህ ክፉ የዓለም ዝንባሌ እንደ ክፋት ብቻ ሳይሆን እንደ ሞኝነትም የሚያሳይብን ነው፤ማንኛችንም ሰዎች ‹‹ሰው ማጥፋት ይሻላል ወይስ ማዳን›› ተብለን ብንጠየቅ መልሳችን ምን እንደሚሆን ይታወቃል።

ነገር ግን ኣንፈጽመውም፣ ሞኝነት የሚያሰኘውም እዚህ ላይ ነው፤ የሚጠቅመንንና የመሰከርንለትን ትተን የሚጐዳንንና፣ ያልመሰከርንለትን እንፈጽማለንና ነው።

ስለሆነም በሕይወት እንዲኖር የተፈጠረውን ሰው በሕይወት የመኖር መብቱን ከመንፈግ መቆጠብ የኣዲሱ ዓመት ትልቁ ኣጀንዳ ኣድርገን ብንወስድ ለሁላችንም ይበጀናልና እንቀበለው እንላለን።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን! ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት!

ሰው በሕይወት እንዲኖር በእግዚአብሔር ሲፈጠር እግዚአብሔርን የሚፈልግበትና የሚያገኝበትን ዕድሜና ዘመንም እንደተሰጠው ከተጠቀሰው ክፍለ ንባብ እንገነዘባለን፤ መቼም እግዚአብሔር ሁሉን የፈጠረ በስራ ለስራ እንደሆነ የምንስተው ኣይሆንም፤ እግዚአብሔር ዕድሜና ዘመን ለሰዎች ሲሰጥ ሊሰራበት ነው፤ ስራውም መንፈሳዊና ዓለማዊ ነው፤ ተደምሮ ሲታይ ደግሞ ለሰው ጥቅም የሚውል ነው።

እኛ ሰዎች በተሰጠን ዕድሜና ዘመን በመንፈሳዊው ስራችን እግዚአብሔርን ፈልገን እንድናገኝ ተፈጥረናል፤ እሱን ማግኘት የማይቻል የሚመስለን ካለንም እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ኣይደለም ተብለናልና በመንፈስ ከፈለግነው በመንፈስ እንደምናገኘው መጽሓፉ ያስረዳናል፤ስለሆነም በተሰጠን ዘመን ይህንን ስራ መስራት ይኖርብናል።

በሌላ በኩል ለኑሮኣችን የሚያስፈልገንን ፍጆታ በበቂ ሁኔታ እንድናገኝ ላባችንን ኣንጠፍጥፈን መስራት ይገባናል፤ ይህም ከሰራን ያለጥርጥር የምናገኘው ነው፤ ሁለቱም የጐደሉብን በኛ ኣስተሳሰብ፣ ኣሰራርና ኣጠቃቀም እንጂ እግዚአብሔር ሳይፈቅድልን ቀርቶ ወይም ነፍጎን ኣይደለም፤ እግዚአብሔር የሰጠን ምድር በልዩ ልዩ ሀብተ ጸጋ የተሞላች እንደሆነች፣ የምንረግጠው መሬትም ወደ ሀብት መቀየር እንደሚቻል የተረጋገጠ ነው።

ነገር ግን እኛ በምንራመድበት በእግራችን ሥር ያለውን ሀብት ትተን በሩቅ ያለውን ስንመለከት ሁሉን ያጣን ሆነን በችግር ወድቀን እንገኛለን፤ በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን በኣሁኑ ጊዜ እየተፈታተነን ያለው ይኸው የተሳሳተ እሳቤ ነው።

ኢትዮጵያ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ኣድርገን በማመን በእኩልነት፣ በኣንድነትና በስምምነት ከመጠቀም ይልቅ የኔ ነው ያም የኔ ነው በሚል ኣባባል ምን ያህል ዋጋ እየተከፈለ እንደሆነ እያየን ነው፤ ይህ ግለኝነት ያየለበት ኣስተሳሰብ ገታ ኣድርገን በእኩልነትና በኣብሮነት የሚያሳድገንን ኣስተሳሰብ በእጅጉ ይጠቅመናል፤ ይህንንም የኣዲሱን ዓመት ምርጥ እሳቤ ኣድርገን ብንወስድ የተሻለ መግባቢያ ሊሆን ይችላል፤ ኣዲሱ ዓመት በኣዲስ እሳቤ ካላጀብነው ኣዲስ ሊሆን ኣይችልምና ነው፤ ስለሆነም ኣዲሱን ዓመት መልካም በሆነ ኣዲስ ኣሳብ ፣እግዚአብሔርንና ሰውን በሚያገናኝ ቅዱስ ተግባር፣ በልማት፣ በሰላም፣ በፍቅር፣ በዕርቅና በስምምነት እንድንቀበለው ወቅታዊ ጥሪያችን ነው።

 

በመጨረሻም ዲሱ ዓመት ለሀገር ሰላምና ልማት፣ ለሕዝቦች ኣንድነትና ስምምነት እንደዚሁም ኣለመግባባትን በፍትሕና በዕርቅ ለመፍታት ከልብ የምንተጋበት መልካም የስኬት ዘመን እንዲሆንልን እንጸልይ፣ በዚህም መላ ሕዝባችን ጠንክሮ እንዲሰራ ለመላ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ ኣባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፤

እግዚአብሔር ኣምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ኣሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣

አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ