የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም ፈተና ከሆነ ሰነባብቷል። ዓለም ለዕድገት ብሎ ባመጣቸው ኢንዱስትሪዎች አማካኝነት ወደ ከባቢ በለቀቃቸው በካይ ጋዞች የፕላኔታችንን ፈተና እያበዛ ነው።
የወደፊቱን አስቦ እንዲጓዝ አዕምሮ የተሰጠው የሰው ልጅ ለአጭር ጊዜ ብልፅግና የፈጠራቸው የኢንዱስትሪ ዘላቂ እና የማይታጠፍ ቀውስ ፈጥሯል።
ያለፈው የረንጆች ዓመት (2024) የዓለም ሙቀት መጠን መመዝገብ ከተጀመረበት ከ1850 አንሥቶ በታሪክ ከተመዘገቡት ሁሉ እጅጉን ሞቃታማ ዓመት ሆኖ አልፏል።
ከ2015 እስከ 2024 ያሉት አሥር ዓመታት ደግሞ እስከ ዛሬ ከተመዘገቡት አሥር ዓመታት ሁሉ እጅግ ሞቃታማ ጊዜ እንደነበረም የተመድ ሪፖርት ያመላክታል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው አማካይ የሙቀት መጠን ከኢንዱስትሪ በፊት (ከ1850 - 1900) ከነበረው አማካይ የሙቀት መጠን በላይ ወደ 1.55 ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍ ብሏል።
ይህም 2015 በፓሪስ ስምምነት ከተቀመጠው የ1.5 ድግሪ ሴልሺየስ መብለጥ የቻለ ሲሆን፣ ሁኔታው ምድራችን ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል።
በነዚህ ዓመታት ውቅያኖሶች ከምድር ከሚወጣው ሙቀት ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሆነው የሰበሰቡ ሲሆን፣ ይህም የውቅያኖሶች ሙቀት በታሪክ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል።
ይህ የውቅያኖስ ሙቀት መጨመር የዓለም ሙቀትን በቀጣይነት ከፍ እያደረገ ከመሆኑም በላይ፣ በረዶዎችን በማቅለጥ የባሕር ወለል እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ሙቀት ምድር ለሰው ልጆች የሰቆቃ ቦታ እያደረጋት ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ አስከትሏል።
ኃይለኛ እና ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ የሙቀት ማዕበል፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ድርቅ እንዲሁም ኃይለኛ አውሎ ነፋስ እና ጎርፍ የችግሮቹ ማሳያዎች ናቸው።
በከፍተኛ ሙቀቱ ምክንያት የሚቀልጠው በረዶ የባሕር ከፍታን እየጨመረ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት በበርካታ ሀገሮች አውዳሚ ጎርፍ እና ማዕበል እየተከሰቱ ይገኛሉ።
የውቅያኖስ መሠረቶች (Coral reefs) እየተጎዱ በመሆናቸው በባሕሮች ውስጥ የሚገኙ ዝርያዎች በመኖሪያ አካባቢያቸው ላይ በሚከሰቱ ለውጦች ሳቢያ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል።
በዚህም መሠረት የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ የምግብ እጥረትን፣ በሽታን፣ ሞት እና ጭንቀትን እያስከተለ ያለ ከኑክልየር የባሰ አውዳሚ እየሆነ ይገኛል።
ያለ ጥፋቷ አየተቀጣች ያለችው አፍሪካ
አፍሪካ ይህን ሁሉ ውድመት እያስከተለ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ የምታበረክተው አስተዋጽኦ ከ4 በመቶ ያነሰ እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ።
ይሁን አንጂ ከ1960ዎቹ ወዲህ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የአፍሪካ የግብርና ምርታማነት 34 በመቶ ቀንሷል፤ ይህ ደግሞ ሕይወቱን በግብርና ላይ ለመሠረተው ከ60 ከመቶ ለሚልቀው የአፍሪካ ሕዝብ ከባድ ፈተና ሆኗል።
በየዓመቱ 500 ሺህ ሔክታር የአፍሪካ መሬት በጎርፍ የሚታጠብ ሲሆን፣ ይህም ሥነ-ሕይወታዊ ሀብት እንዲጠፋ እና የካርቦን ልቀት እየጨመረ እንዲሄድ እያደረገ ይገኛል።
ቃሉን ያላከበረው ዓለም
ዓለም የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን አስፈሪ ጉዳት ተረድቶ በፓሪስ በመሰብሰብ ቢያንስ ችግሩ ካለበት በላይ እንዳይሄድ ለማድረግ የጋራ ስምምነት ላይ ከደረሰ አሥር ዓመታት ቢያልፉም እስከ አሁን ግን ቃሉን አላከበረም።
በ2015 በፓሪስ የአየር ለውጥ ጉባኤ ላይ የተደረሰው ‘የፓሪስ ስምምነት’ የዓለም ሙቀት መጠን ከ1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንዳይሆን መጠበቅ ነበር።
ይህን ከግብ ለማድረስ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገሮች ለአዳጊ ሀገሮች የአየር ንብረት ለውጥ መስፋፋትን ለመቀነስም ሆነ ከሁኔታዎች ጋር ለመላመድ የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ለማቅረብ ተስማምተው ነበር።
አዳጊ ሀገራት ቀውሱን የሚቋቋሙባቸውን የቴክኖሎጂ ዕድገትን እና ሸግግርን መደገፍ እንዲሁም ለአደጋ የተጋለጡ ሀገራት የአየር ንብረት ዕቅዳቸውን እንዲተገብሩ ለማገዝ የአቅም ግንባታ ድጋፍን ለማድረግ በፓሪስ ቃል ተገብቷል።
የተጠቀሱትን ግቦች ለማሳካት በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገሮች በማደግ ላይ ላሉ ሀገሮች በየዓመቱ 100 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለመስጠትም ቃል ገብተዋል።
ይሁን እንጂ በተገባው ቃል መሠረት እስከ 2030 ድረስ 3 ቲሪሊዮን ዶላር መቅረብ የነበረበት ቢሆንም እስከ አሁን ግን የተገኘው ገንዘብ 30 ቢሊዮን ዶላር (20 በመቶው) ብቻ ነው።
የመፍትሔ ሐሳብ ይዛ ወደ ተግባር የገባችው አፍሪካ
የተገባው ቃል የታጠፈባት አፍሪካ እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም። በአንድ በኩል ዓለም ቃሉን እንዲያከብር እየጠየቀች በሌላ በኩል የራሷን የመፍትሔ እርምጃዎች መውሰዷን ቀጥላለች።
ለመፍትሔውም ታዳሽ ኃይል እና አረንጓዴ ቴክኖሎጂ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርና እና የውኃ አስተዳደር፣ እንዲሁም የፓን-አፍሪካ ትብብር እና የፖሊሲ አድቮኬሲ ላይ አተኩራ እየሠራች ትገኛለች።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ፣ የኮንጎ ደን ጥበቃ፣ የኬንያ ታዳሽ የኃይል ማመንጫ ቃል ኪዳን፣ ታላቁ አረንጓዴ ግድግዳ ኢኒሼቲቭ እና እያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር በፖሊሲ ደረጃ እየተገበራቸው ያሉት የአየር ንብረት ለውጥ መከለያከያ ዘዴዎች የዚህ ተነሳሽነት ማሳያዎች ናቸው።
በ2023 በኬንያ አስተናጋጅነት የተካሄደው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፎርም፣ የዕዳ ማቅለያ እና የአረንጓዴ ልማት አጀንዳ አስፈላጊነትን የሚያጎሉ 11 ነጥቦችን በዝርዝር በማስቀመጥ የተግባር ጥሪ ያቀረበ ሰነድ አዘጋጅቶ ነበር።
በተጨማሪም በናይሮቢ ስምምነት መሠረትም አፍሪካ የተገባው ቃል እንዲከበር እና እየደረሰ ላለው ጉዳት ካሳ እንዲከፈል በ27ኛው የአየርን ንብረት (COP27) ጉባኤ ላይ አቋሟን አንጸባርቃለች።
2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉበኤ (African Climate Summit 2) ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
በጉባኤው ላይ የአፍሪካ መሪዎች እና በዘርፉ ላይ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ ከ20 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል።
በጉባኤው ላይ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እየሠራቻቸው ያሉ ሥራዎች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚዳሰሱ ሲሆን፣ ዓለም ለመፍትሔው በጋራ እንዲቆም ጥሪ ይቀርባል።
አዳዲስ ጥምረቶችን ማሳደግ እና በአፍሪካ መሪነት የተጀመረውን የመድትሔ ሐሳብ ወደ ተግባር ለመለወጥ ተጨማሪ ገንዘብ የሚገኝበትን አቅጣጫም መቀየስ የጉባኤው ሌላኛው ዓላማ ነው።
በለሚ ታደሰ
#etv #EBC #ebcdotstream #COP27 #climatesummit2025 #AfricanClimateSummit