የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ መጪውን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ የክልሉ መንግሥት የይቅርታ አዋጁን መስፈርት ላሟሉ 853 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን አስታውቀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፣ ይቅርታ የተደረገላቸው የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መልካም ሥነ-ምግባር ያሳዩ እና በሕግ የተደነገገውን የይቅርታ መስፈርት በማሟላት በክልሉ የይቅርታ ቦርድ ተጣርቶ የቀረቡ ናቸው።
ይቅርታው ከተደረገላቸው ታራሚዎች መካከል 841 ከእስር የሚፈቱ ሲሆን፣ ቀሪ 12 ታራሚዎች ደግሞ የእስራት ጊዜያቸው የተቀነሰላቸው መሆኑን ርዕሰ መስትዳድሩ አስረድተዋል።
ከታራሚዎች መካከል 54ቱ ሴቶች መሆናቸውንም አመላክተው፣ የይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑ የሕግ ታራሚዎች የይቅርታን እሴት ተላብሰው ሰላም ወዳድ፣ ለሕግ ተገዥ እና አምራች ዜጋ በመሆን የበደሉትን ኅብረተሰብ ማገልግል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ኅብረተሰቡም በይቅርታ የተለቀቁ የሕግ ታራሚዎች መልካም እና አምራች ዜጋ ይሆኑ ዘንድ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
በተመስገን ተስፋዬ