Search

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ የዘመን መለወጫ መልዕክት

ረቡዕ ጳጉሜን 05, 2017 51

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። 

“በዚህ ተስፋ ድነናል።” ሮሜ 8፡24 

መላው ምዕመናንና የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ  

ከአገራችሁ ውጪ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን 

እንኳን ለ 2018 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም አደረሳችሁ። እንኳን ከዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ማርቆስ 2018 ዓ.ም አዲስ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡ 

አዲሱን ዓመት የምናከብረው በዓለም አቀፍ ደረጃ ቤተክርስቲያን ኢዩቤልዩን እንድናከብር በምትጠራን ወቅት ነው። የተስፋ ተጓዦች መሆናችንን እንድንገነዘብ በተጋበዝንበት ወቅት ነው። ስለዚህ አዲስ ዓመትን በኢዩቤልዩ መንፈስ ማክበር ትልቅ ጸጋ ነው።  በብሉይ ኪዳን ዘመን ሕዝበ እግዚአብሔር የኢዩቤልዩ ዓመትን በምስጋና፣ በደስታ፣ በነፃነትና በፍትሕ መንፈስ ያከብሩት ነበር። ዕዳዎች የሚሰረዙበት፣ ሰዎች ወደ ቤታቸው የሚመለሱበት ወቅት ነበር። ያ የጥንቱ በዓል ዛሬም ትልቅ ቦታ አለው። በመሆኑም የማይነጥፍ መንፈሳዊ ምንጫችን ነው። የጊዜ ባለቤት የሆነውን አምላክን የምናስታውስበት፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀምን የምንማርበት ልዩ የጸጋ ስጦታ ነው። 

ዛሬ ስናመሰግን ነገን በክርስቶስ ተስፋ እየጠበቅን ነው። ነገን ደግሞ ስንቃኝ ዛሬ እንዴት መኖር እንደሚያስፈልገን ብርሃን ስለሚሰጠን ነው። ምክንያቱም እምነታችን ተስፋ ለምናደርጋቸው ነገሮች ማረጋገጫ እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ 

ያስተምረናልና ነው። ተስፋ፣ እምነትና ፍቅር የማይነጣጠሉ መንፈሳዊ ኃይላት ናቸውና። ያለፈውን በምስጋና የምንመለከተው የእግዚአብሔርን ሥራዎች ለማየት ስንችል ነው። 

በእምነት መነጽር ያለፈውን ማየት ለንስሐም ይጋብዘናል። ምን መልካም ተሠራ? እንደምንለው ሁሉ ምን ስህተት ተፈፀመ? ብሎ መመርመር ጥበብ ነው። ለዚህም ነው ቅዱሳት መጻሕፍት በተደጋጋሚ “ኑ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ” በማለት ያስተምሩናል። አዲስ ዓመትም መልካምና የሠመረ የሚሆነው ወደ እግዚአብሔር መመለስ ለሚለው ጥሪ ተገቢውን ትኩረት በሰጠን መጠን ነው። ወደ እግዚአብሔር መመለስ ያለፉትን ቁስሎች ያክማል፣ ያላየነውን እንድናይ ያደርገናል። 

ለመለኮታዊ ፍቅር ቦታ ሳይሰጡ እውነተኛ ደስታን ማግኝት አይቻልም። ዛሬም ሆነ ነገ ወደ እውነተኛ ደስታ የሚያቀርበን የረጅምና የአጭር ጊዜ እቅዳችንን ከአምላክና ከባልጀራ ፍቅር ጋር ስናዋሕደው ነው። ነገን በእግዚአብሔር ፍቅር መነጽር ማየት ማለት የሕይወትን አቅጣጫ ማስተካከል ማለት ነው። የተስፋ ተጓዥ መሆን ነው። ከግልና ጊዜያዊ እርካታዎች ወጥቶ ለወንድምና ለእህት ደስታ እራስን መስጠት ማለት ነው። የጻድቅ ደስታው የሚመሠረተው በሌሎች ደስታ ላይ እንደመሆኑ መጠን እኛም የዚህ ሱታፌ አባላት የምንሆነው ከራስ ወዳድነት ወጥተን ለሌሎች ደስታ ስንደክም ነው። እንዲህ ዓይነቱ ድካም ጤናማ ድካም መሆኑን በዚያ ያለፉት ያስተምሩናል። እንዲህ ዓይነቱ ድካም ሰላምና ደስታን እንደሚሰጣቸው ያሳዩናል።  

ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ፊሊጲሲዮስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ስለ ደስታ ደጋግሞ አስተምሯል። አንባቢዎቹና አድማጮቹ ሁልጊዜ ደስ እንዲላቸው ያሳስባቸዋል። ቅዱስ ጳውሎስ ስለራሱ ምቾት የሚለፋ ሰው ቢሆን ኖሮ እንዲህ ዓይነት ጥሪን ባላስተላለፈ ነበር። በእስር ቤት ሆኖ ይህና ይህ ነገር ጎደለብኝ በማለት ማጉረምረምን በመረጠ ነበር። ነገር ግን እምነት፣ ተስፋ እና ፍቅር እውነተኛ እንቁዎች እንደሆኑ አምኖ ለሌሎችም እንዲዳረስ ሕይወቱን ሰጠ። ሌሎች ወገኖቹ አይሁዳውያንም ሆኑ ግሪካዊያን፣ ሃብታሞችም ይሁኑ ድሆች፣ ወንዶችም ይሁኑ ሴቶች፣ የዚህም ቋንቋ ሆነ የዚያኛው ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ ሁሉም በእምነት፣ በተስፋ እና በፍቅር ደስተኛ እንደሚሆኑ በማመን አገለገለ። 

በወንጌል ብርሃን ማቀድ ግለሰብንም ሆነ ቤተሰብን፣ መስሪያ ቤትንም ሆነ ማኅበራትን በበረከት ይሞላል። ሁለንተናዊ እድገትን ያመጣል። ከአሮጌው ሰውነት ወደ አዲሱ ሰውነት ያሸጋግረናል። የሰው ጥበብ ብቻውን ከሆነ ከተወሰነ ከፍታ በላይ መጓዝ አይችልም። የእግዚአብሔር ጥበብ ግን ከተወሰነው ከፍታ በላይ ያስኬደናል። እነሆ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶሰን ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት በፊት ለሰው ልጆች ያመጣውን የምናስታውስበት ዘመን ተሰጥቶናል። ሁላችንም ለዓመቱ መጀመሪያ ትልቅ ቦታ ብንሰጥ ዓመቱን በሙሉ እናመሰግናለን። ከሁሉ የሚበልጠው ስጦታ ይህ ነውና እናመስግነው። ልባችን ሃብታችን ክርስቶስ ከሆነ ለምስጋናም ሆነ ለንሰሐ ሁልጊዜ ዝግጁዎች እንሆናለን። 

ክርስቶሳዊ ኢዩቤልዩ ያለውን ልጅ ታሪክ ቀይሮታል። የክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ዓለምን የምንመለከትበትን መንገድ አቅንቶታል። በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ አማካኝነት የግልና የጋራ ታሪካችን ተለውጧል። ክርስቶሳዊ ኢዩቤልዩ የእግዚአብሔር ፍቅር በሙላት በዓለም ላይ መገለጡን እንድናከብር ይጋብዘናል። እግዚአብሔር ዓለምን እስከምን ድረስ እንደወደደ የምንገነዘብበት ዘመን ነው። እነዚህ ጊዜ፣ ወራት፣ ሳምንታትና ቀናት በእግዚአብሔር መንግስት ብርሃን በየዕለቱ የምስጋና ጊዜን ይሰጡናል። የወንጌልን የምስራች እንድናስቀድም ያሳስቡናል። እኛ ልባችን ወደ ተለያዩ ጉዳዮች ሲያተኩር ምስጋናን እንረሳ ይሆናል። መሰናክሎችን የምናስወግደው ወይንም የምንሻገረው ለሚበልጠው ቅድሚያ ስንሰጥ ነው። ከነዚህም ትልቁ ስጦታ ሕይወት መሆኗን ስንገነዘብ ነው። አዲስ ዘመንን የምናከብረው ሕይወትና ጊዜ የተሳሰሩ ቁምነገሮች ስለሆኑ ነው። ፈጣሪያችን እና አዳኛችን ላለፈውም ሆነ ለሚመጣው ሕይወትንና ዘመንን ይሰጠናል። 

ወደ ሰላም በሚወስዱ ሀሳቦች፣ እቅዶች፣ ንግግሮች በግላችን እናክብር ። አዲሱን አመት በዚህ እንጀምር። በወንጌል ተስፋ ላይ የተመሰረቱ ሀሳቦችን፣ ንግግሮችን፣ ውይይቶችን የምናከናውንበት አዲስ አመት ይሁንልን። ንግግራችን የሰዎችን ቁስሎች ይፈውሱ፣ ወደእርቅና አንድነት ይምሩን። የምቀኝነትን እና የጥላቻን መንስኤዎች የምንፈልግበትና መፍትሄ የምናመጣበት አመት ይሁንልን። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን የምናስተውልበት ዘመን ይሁንልን።  

ንስሐና ለውጥ የመልካም ሕይወትና የእውነተኛ ደስታ መሰረት ናቸው ። አዲሱ ዓመት ሰላምንና ደስታን እንዲያመጣልን ወደ ጌታ እንመለስ፤ በልባችን ዘወትር እንያዘው፣ ወደተግባርም ለመለወጥ እንድንችል የመንፈስ ቅዱስን ጸጋን እንጠይቅ። 

ቅዱስ ጳውሎስ አሮጌው በእውነት እንዳለፈ እንዲሁም አዲሱን ሰውነት እንድንለብስ ያስተምረናል። አዲሱ አመት ይህ በይበልጥ እውን የሚሆንበትን ለማመቻቸት እንትጋ ። አዲሱ ዓመት በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ እና ጥበብ የተሞላ ሰውነት ነው። ዛሬንና ነገን በልዩ መነጽር እንድናይ የሚያስችለን የእግዚአብሔር መንፈስ ነው። መንፈስ ቅዱስ የመልካም ሕይወት፣ የስጦታዎች ሁሉ ባለቤት ነውና የንስሀንና የዕምነትን ጸጋ እንዲሰጠን ሳንታክት እንጸልይ። የእግዚአብሔርን ፍቅር በልባችን ውስጥ የሚያፈሰው መንፈስ ቅዱስ ነው። ፍቅርን በተመለከተ ድክመታችንን እንድናሸንፍ፣ መልካሙን እንድናሻሽል ኀይል የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ ነው። 

የሰው ልጅ ብዙውን ጊዜ በቁጭት እና በስጋት የተሞላ ይመስላል፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ስናልፍ ስለ አዲስ ዘመን መልካም ማሰብ ይከብዳል። አዲሱም ዘመን ሊያስፈራ ይችላል። ጊዜ ጸጋ የሚሆነው በእግዚአብሄር የተባረከ ሲሆነ ነው። አለበለዚያ ጊዜ ሊያስጨንቀን ይችላል። በትካዜ እና በስጋትም ሊያቆየን ይችላል። ሆኖም ከስጋትም ሆነ ከትካዜ የምንወጣው የጊዜ ፈጣሪ እና የጊዜ ፈዋሽ አምላክ ወደ ዘላለማዊ ሰላም ሲያመጣን ነው። ሰላምና ፍቅር ሲሰፍኑ ደስ ይላል። ጭንቀት እና ስጋት ኀይል አይኖራቸውም። በርስቶስ ትንሳኤ በዘመናት የማይቀየሩ እምነትን፣ ፍቅርን እና ተስፋን እናውጃለን። ዳግም መምጣቱንም እንመሰክራለን። ሞትና ትንሳኤውን ስናውጅ ስላለፈው እያሰብን ያለፈውን እያስታወስን ነው። ስለ ዳግም ምጻቱ ስንመሰክር የወደፊቱን በተስፋ እየጠበቅን መሆኑን እየገለጽን ነው። ባለፈውና በሚመጣው መካከልም ያለውን ጊዜ ለእግዚአብሔር በአዲሱ ዓመት ለርኅራሄና ለልግስና እንዘጋጅ። 

የተወደዳችሁ ምዕመናን ! 

ሁላችንም በዙሪያችን ያሉትን ወገኖቻችንን እናስታውስ። በጸሎት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መልካም ተግባራት መጽናናትና የተሻለ ሕይወትን እናበርክትላቸው። ፈጣሪ ጌታ አንዳችንም እንድንራብ አይፈልግም። በዘላቂ ሁኔታ ሰዎች ጠግበው የሚያድሩበትን ሁኔታ እንፈልግ ለዚህም ተግተን እንስራ።አዲሱ ዓመት የተሰጠን በጎ ነገሮችን እንድናስብና ለጋራ ጥቅም የሚሆኑ ተግባራትን እንድንፈጽም ነውና ለዚህ እንነሳሳ። አዲሱ ዘመን ለተራቡት፣ለተጠሙት፣ለታሰሩት፣ ለታመሙት፣ ለተሰደዱትና ላዘኑት የሚጽናኑበትና የሚደሰቱበት ጊዜ ይሁንላቸው። በአዲሱ አመት ለእግዚአብሔር ክብር በክርስቲያናዊ ተስፋ ምስክርነታችንን እናጽና ። 

ቸሩ መድኃኔ ዓለም 2018 ዓ.ምን ባርኮልን የሕዳሴ ግድባችንን በሰላም የምንመርቅበት ዓመት እንዲሁም በመላው በኢትዮጵያ አገራችን እርቀ ሰላም ወርዶልን በፍቅርና በህብረት የምንኖርበት ዘመን ያድርግልን፡፡  

ልዑል እግዚአብሔር አዲሱን ዓመት ይባርክልን፣ የሰላም መሳሪያዎች ያድርገን፣ ቃል ስጋ ሲሆን የዓለም ታሪክ ሲቀየር፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነችው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት ዘወትር ከእኛ አይለይ፤ በድጋሚ ሁላችሁንም እንኳን ለ2018 ዓ∙ም በሰላም አደረሳችሁ። 

ልዑል እግዚአብሔር ሀገራችንን ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክልን ! 

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ 

ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን 

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት