Search

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለ745 ታራሚዎች ይቅርታ ተደረገ

ሓሙስ መስከረም 01, 2018 35

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ 745 የሕግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገልጸዋል።
ይቅርታ ከተደረገላቸው ታራሚዎች መካከል 720ዎቹ ወንዶች ሲሆኑ 25ቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።
ውሳኔው ታራሚዎቹ ካቀረቡት የይቅርታ ጥያቄ በመነሳት በይቅርታ አዋጅ፣ ደንብ እና መመሪያዎች መሠረት የክልሉ የይቅርታ ቦርድ ጥያቄዎችን መርምሮ በመስፈርቱ መነሻ ለክልሉ መንግሥት ካቀረበ በኋላ የተላለፈ መሆኑም ተገልጿል።
የይቅርታ ተጠቃሚ የሆኑት ግለሰቦች በማረሚያ ተቋም በነበራቸው ቆይታ በመልካም ሥነ ምግር መታነጻቸውን የሚያረጋግጥ በቂ መረጃ ከየደረጃው ከሚገኙ የፀጥታ ተቋማት የቀረበላቸው መሆኑም ተረጋግጧል።
ከእስር የሚለቀቁት ታራሚዎች ከዚህ በኋላ ለኅብረተሰቡ የስጋት ምንጭ ሳይሆኑ ሰላምን የሚሰብኩ፣ አምራች እና ሕግ አክባሪ ዜጎች እንዲሆኑ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
ኅብረተሰቡም የእነዚህን ዜጎች መታረም እና መታነፅ ተገንዝቦ እንዲቀበላቸው እና በቀጣይነትም በየደረጃው ወንጀልን በመከላከል እና የሕግ የበላይነትን ይበልጥ ለማረጋገጥ የተቀናጀ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በሰለሞን ባረና