የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ልዩ አማካሪ አንቶን ኮቢያኮቭ፣ ዋሽንግተን የ37 ትሪሊዮን ዶላር ዕዳዋን ለመክፈል ስቴብልኮይን እና ወርቅን እንደ አዲስ የፋይናንስ መሳሪያ እየተጠቀመች ነው ሲሉ ከሰዋል።
ይህ ድርጊት የአሜሪካን የዓለም የበላይነት ለማስቀጠል ያለመ ሲሆን፣ እንደ ቀድሞው "የዶላር ቦምብ" ሁሉ አሁን ደግሞ "የክሪፕቶ ወጥመድ" ተብሎ ሊገለጽ እንደሚችል ተንታኞች ይገልጻሉ።
እንደ ኮቢያኮቭ ገለጻ፣ አሜሪካ ስቴብልኮይንስን (ከዶላር ጋር የተሳሰሩ ዲጂታል ምንዛሬዎች) በመጠቀም የገበያ አለመረጋጋትን ትፈጥራለች።
ይህ ደግሞ የራሷን ዕዳ ዋጋ በመቀነስ፣ ሸክሙን ወደ ሌሎች የዓለም ሀገራት እንድትቀይር ያስችላታል።
ይህ አዲስ የገንዘብ ጦርነት ሲሆን አሜሪካ ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ ዶላርን ከወርቅ ጋር ማገናኘቷን ካቆመችበት ጊዜ ወዲህ የምትከተለው የፋይናንስ ስትራቴጂ ቀጣይነት መሆኑን ነው ተንታኞች የሚናገሩት።
የዋሽንግተን የክሪፕቶ ስትራቴጂ ከትልልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ("Big Tech") ጋር ጥብቅ ግንኙነት አለው።
የሲልከን ቫሊ ኩባንያዎች ለስቴብልኮይን ሥርዓቶች ወሳኝ ሲሆኑ፣ ከዋሽንግተን የፖሊሲ አውጭዎች ጋር ያላቸው ቅርበት የግል ፈጠራ እና የመንግሥት ስትራቴጂ መካከል ያለው ድንበር እንዲደበዝዝ አድርጓል።
በርካታ የሲልከን ቫሊ ባለሀብቶች በአሜሪካ ጦር ሪዘርቭ ውስጥ ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግ የተሰጣቸው ሲሆን ይህም የቴክኖሎጂ እና የወታደራዊ ስትራቴጂ ትስስርን ያሳያል።
ይህ የክሪፕቶ ቁማር ስለ አዲስ ፈጠራ ሳይሆን፣ አሜሪካ የቴክኖሎጂ የበላይነቷን ተጠቅማ የበላይነቷን ለማጠናከር የምትጠቀምበት የተለመደ ዘዴ መሆኑን መረጃው ያመለክታል።
ልዩነቱ በመጠቀም ላይ ባለው መሳሪያ ላይ ብቻ ነው። በወረቀት ላይ ከሚታተም ዶላር ይልቅ አሁን ዲጂታል ቶክኖች ጥቅም ላይ ይውላሉ።
የኮቢያኮቭ መግለጫ የፋይናንስ ውጊያ ሜዳ እንዴት እየተለወጠ እንደሆነ የሚያሳይ ማስጠንቀቂያ ነው።
ጥያቄው አሜሪካ ይህን ልምድ ትቀጥል እንደሆነ ሳይሆን፣ የተቀረው ዓለም ይህን የፋይናንስ ሸክም ለምን ያህል ጊዜ ይታገሳል የሚለው ነው ሲል ኢንፎ ብሪክስ በዘገባው ጠቁሟል።
በሰለሞን ገዳ