Search

አዲሱ ዓመት ከተስፋ ወደ ብርሃን የተሻገርንበት በመሆኑ ደስታችን ድርብ ነው - ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ

ሓሙስ መስከረም 01, 2018 88

አዲሱ ዓመት የድል ንጋት የሆነልንን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቁርጠኛ አመራር በሕብረት አጠናቅቀን ከተስፋ ወደ ብርሃን የተሻገርንበት በመሆኑ ደስታችን ድርብ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሀገራችን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የነበራትን ምኞት ወደ ጂኦፖለቲካ አቅም የቀየረ ነው ብለዋል አቶ ሽመልስ የ2018 የኢትዮጵያ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የለውጡ መንግሥት ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ህዝቦቻችን እረፍት እንዲያገኙ አድርጓል ብለዋል።

ሀገራችን እንድታንሰራራ የተለያዩ ትላልቅ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ በግብርና ልማት፣ በኤክስፖርት ምርቶች ማስፋት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በኮሪደር ልማት፣ በቱሪዝም፣ በዲጂታላይዜሽን እና በፕሮጀክት አፈፃፀም በርካታ ስኬቶች መገኘታቸውን አክለዋል።

አዲሱ ዓመት በሁሉም መስኮች የተጀመሩ ኢኒሼቲቮችን በማስቀጠል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የምንተጋበት ይሆናል ነው ያሉት አቶ ሽመልስ በመልዕክታቸው።

ያለፈው ዓመት በክልል ደረጃም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ የሆነ ትውልድ ለማፍራት፣ አዳጊ የህዝብ ኢኮኖሚ ለመፍጠርና የጎለበተ ሥርዓት ለመገንባት ሶስት ዓበይት ግቦች ተቀምጠው ጠንካራ መሰረት የጣልንበት ነው ብለዋል።

አዲሱን ዓመት ስንቀበል በቀጣይ ጥንካሬዎችን በማስፋት እና ድክመቶችን በመቅረፍ የልማት ሥራዎች እና ውጥኖችን በጥራት እና በፍጥነት ለመከወን ቁርጠኝነታችንን በማደስ ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳደሩ።

በሃይማኖት ከበደ

#EBCdotstream #EthiopianNewYear #2018EC