Search

የጥቁር ወርቁ በረከት ከደቡብ ምድር

ዓርብ የካቲት 27, 2018 87

ኢትዮጵያ በምድር ሆዷ የቋጠረችው የተፈጥሮ ጸጋ ዛሬ ለሀገራዊ ብልጽግና ትልቅ ስንቅ እየሆነ ይገኛል።
በመደመር መንግሥት ልዩ ትኩረት የተሰጠው የማዕድን ዘርፍ፣ በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚመረተው የድንጋይ ከሰል የኢኮኖሚው አዲስ ሞተር ሆኖ ብቅ ብሏል።
ይህ "ጥቁር ወርቅ" ተብሎ ሊጠራ የሚችለው ማዕድን፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በስፋት እንደሚመረት ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ያነሱት የክልሉ ማዕድን ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር መርክነህ ቦጋለ፤ ምርቱ ከዉጭ የሚገባዉን ከመተካቱ ባሻገር ዘርፉ በክልሉ ለ11 ሺህ 300 ወጣቶች የስራ ዕድል ስለመፍጠሩም ጠቅሰዋል።
ባለፉት ሥድስት ወራት ብቻ ከተገኘው የማዕድን ገቢ 95 በመቶውን ድርሻ በመያዝ አስገራሚ ስኬት አስመዝግቧል።
የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በወላይታ ዞን ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ውስጥ ብቻ 81 ሚሊዮን ቶን የሚሆን የከሰል ድንጋይ ክምችት ማገኘቱን አረጋግጧል፡፡
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ለድንጋይ ከሰል ገቢ ምርት በዓመት ታወጣ የነበረውን ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል።
ዛሬ ፋብሪካዎች ግብዓታቸውን ከሀገር ውስጥ እያገኙ ነው፤ ይህም "የገቢ ምርትን በሀገር ውስጥ መተካት" የሚለውን ራዕይ በተግባር አሳይቷል።
በአጠቃላይ፣ የድንጋይ ከሰል ልማት የኢንዱስትሪዎች ማነቃቂያ ከመሆኑም ባለፈ፣ ማዕድኑ በሚወጣባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ማኅበረሰቦች የኑሮ መሻሻልንና የተስፋ ብርሃንን ይዞ መጥቷል።
በሲሳይ ደበበ