Search

የአዲስ አበባ ድንጋጌ አፍሪካ በዓለም የአየር ንብረት ያላትን የመሪነት ሚና የሚያፀና ነው - ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ሕብረት

ሓሙስ መስከረም 01, 2018 84

ባለፉት ሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የአፍሪካ አየርን ንብረት ጉባኤ የአፍሪካ መግለጫን በማጽደቅ ተጠናቀቀ፡፡

ጉባኤው ሲጠናቀቅ ዓለም ለአፍሪካ መር የአየር ንብረት መፍትሄዎች ትኩረት እንዲሰጥ የሚጠይቅ የአዲስ አበባ መግለጫን በይፋ አጽድቋል፡፡ 

ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አፍሪካ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ገፈት ቀማሽ ብቻ ሳትሆን የመፍትሄው መሪ ተዋናይ መሆኗን በግልጽ መልዕክቷን ያስተላለፈችበት መሆኑን ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ሕብረት ባወጡት የጋራ መግለጫም አስታውቀዋል።  

በመግለጫው፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአፍሪካን የአየር ንብረት ተነሳሽነት እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለመተግበር እንዲሁም የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በገንዘብ ለመደገፍ ተግባራዊ እርምጃ እንዲወስዱ ተጠይቋል።

የአፍሪካ መሪዎች አፍሪካ በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔዎችን በአፍሪካ የሚመሩ መፍትሔዎችን ለመውሰድ ቃል ገብተዋል።

አፍሪካ ለዓለም በጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ ብቻ ሳትሆን የመፍትሄ ምንጭ እና መሪ መሆኗን ጠንካራ መልዕክት እንዳስተላለፈች ተመላክቷል።

የአየር ንብረት ችግሮችን ለመቋቋም በተፈጥሮ ላይ የተመሰረቱ መፍትሔዎች ወሳኝ መሆኑን የጠቆመው ጉባኤው፣ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ እንደ አህጉራዊ ሞዴል ዕውቅና እንዲሰጠው ወስኗል። 

የአየር ንብረት ለውጥ ፍትህን ማረጋገጥ፣ የአፍሪካ መፍትሔዎችን መተግበር እና ቀጣይነት ያለው ብቁ አመራር ችግሩን ለመቋቋም ወሳኞች መሆናቸውን ጉባኤው አስምሮበታል።

መግለጫው የአፍሪካ የደን እና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ መልሶ ማቋቋም ተነሳሽነት፣ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ እና ሌሎችም በአፍሪካውያን የሚመሩ የአየር ንብረት ተነሳሽነቶችን አፈፃፀም ለማሳደግ ጠንካራ እና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል። 

የአየር ንብረት ለውጥ ፍትህን ማረጋገጥ፣ የአፍሪካ መፍትሔዎችን መተግበር እና ቀጣይነት ያለው ብቁ አመራር ችግሩን ለመቋቋም ወሳኝ መሆናቸውን ጉባኤው አስምሮበታል።

በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት በ“Africa Climate Innovation Compact” እና “African Climate Facility” የተሰኙ ኢኒሼቲቮችን ይፋ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ለሀገር በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች 50 ቢሊዮን ዶላር ሀብት በየዓመቱ የማሰባሰብ ስራ እንደሚከናወን ተመላክቷል።

መሪዎቹ በጉባኤው ላይ የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ወደ ስራ ማስገባት የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸውን የገለጸው የጋራ መግለጫው፥ ፈንዱ እዳን ከሚያሸክሙ ብድሮች ይልቅ የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ጠቁሟል። 

በጉባኤው ዓለም አቀፍ አጋሮች የፋይናንስ ድጋፎችን ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

በጉባኤው ላይ 25 ሺህ በላይ ልዑካን የተሳተፉ ሲሆን 240 የጎንዮሽ ሁነቶች እና በርካታ አውደ ርዕዮች መካሄዳቸውን ያመለከተው መግለጫው፥ ይህም አፍሪካ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ እና ኢኖቬሽን የተግባር ማሳያ እንደሆነች መታየቱን አመልክቷል።

መሪዎች በጉባኤው አፍሪካ እ.አ.አ በ2030 በዓለም የታዳሽ ኢነርጂ ኢንቨስትመንት ያላትን ድርሻ ከ2 በመቶ ወደ 20 በመቶ ከፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

የአረንጓዴ ማዕድናት እና ንጹህ የኢነርጂ ተደራሽነት የሚያሰፉ ስትራቴጂዎችን ማጠናከር ሌላኛው ጉባኤው ከስምመነት ላይ የደረሰበት አጀንዳ ነው።

አፍሪካ በብራዚል ቤለም የሚካሄደውን 30ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 30) እየተመለከተች ባለችበት ወቅት የፀደቀው የአዲስ አበባ ድንጋጌ አፍሪካ በዓለም የአየር ንብረት ያላትን የመሪነት ሚና የሚያጸና መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፥ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሄዷል።

 

በለሚ ታደሰ