ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ የተካሄደው 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ (ACS2) የተሳታፊዎች አስደናቂ መስተጋብር የታየበት መሆኑን ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ሕብረት በጋራ ያወጡት መግለጫ አመላክቷል።
በጉባኤው ከ25 ሺህ በላይ የሚሆኑ የመንግሥታት መሪዎች እና ልዑካን፣ ሚኒስትሮች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ሴክተሮች፣ የአካባቢ ጥበቃ ማኅበረሰብ እና የሀገር ውስጥ ተሳታፊዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶች እና የሌሎች የኅበረተሰብ ተወካዮች ላይ መሳተፋቸውም ታውቋል።

በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር (AICC) በተካሄደው ጉባኤ ከአፍሪካ ሀገራት፣ ከቀጣናዊ ድርጅቶች እና ከልማት አጋሮች የተውጣጡ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉባቸው 23 “ፓቪሊዮኖች” ተካሂደዋል።
አረንጓዴ ልማት፣ የካርቦን ልቀትን መቀነስ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ ፈጠራዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ከ43 በላይ ዐውደ ርዕዮች በግሉ ዘርፍ እንደቀረቡበት በመግለጫው ተጠቅሷል።
አፍሪካ መር የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔዎች ላይ ያተኮሩ ከ240 በላይ የጎንዮሽ ውይይቶችም ተካሂደዋል።

ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ(ACS2) አፍሪካ በ30ኛው የዓለም አየር ንብረት ጉባኤ(COP30) ላይ መፍትሔ ተኮር ተሳትፎ የምታደርግበትን አቅጣጫንም አስቀጧል፡፡
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይም ቀጣዩ የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ ጣት ከመጠቋቆም ያለፈ ውጤታማ እና ትብብርን መሰረት ያደረገ እንዲሆን አቅጣጫ ተቀምጧል።

የጉባዔው ስኬት አፍሪካ በ30ኛው የዓለም አየር ንብረት ጉባኤ(COP30) እና ከዚያም በኋላም በሚኖሩት ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ድምጿን ማስተጋባት፣ ውጤቶችን መገምገም፣ መምራት እና ለውጥ ማምጣት እንደምትችል ማረጋገጫ እንደሆነም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን "የአዲስ አበባ መግለጫ"ን ተግባራዊ ለማድረግ እና የሁለተኛው የአየር ንብረት ጉባኤ ውሳኔዎችን እና ተነሳሽነቶች ለመደገፍ አመራራቸውን እንደሚቀጥሉ ተመላክቷል።
በለሚ ታደሰ