Search

ኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ያለብድር መሥራት እንደሚቻል ለአፍሪካውያን አሳይታለች - ናይጄሪያዊው ምሁር ኦዳዪ ኦማሌ

ሓሙስ መስከረም 01, 2018 228

ኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በውስጥ አቅም በመገንባት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ያለብድር እና እርዳታ መሥራት እንደሚቻል ለአፍሪካ ማሳየት ችላለች ሲሉ ናይጄሪያዊ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ኦዳዪ ኦማሌ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡



ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ትንተና የሚያቀርቡት ምሁሩ ከናይጀሪያው አራይዝ ኒውስ የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ወለድ የሚያስከፍለውን የውጭ ብድር ከማፈላለግ ይልቅ ቦንድ አዘጋጀታ ዜጎቿን በማስተባበር የሕዳሴ ግድቡን እውን ማድረጓ ለአፍሪካ ትልቅ ተሞክሮ ነው ብለዋል፡፡



ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፉን የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ግድብ ለመገንባት ዜጎቿን በማስተባበር የተከተለችውን ስልትም አፍሪካውያን ሊማሩበት እንደሚገባ ነው ምሁሩ ያመላከቱት።

አፍሪካ እምቅ የተፈጥሮ ሃብቷን መጠቀም የምትችለው በራሷ አቅም ማልማት ስትችል መሆኑን አንስተው፤ ለዚህም ኢትዮጵያ ምሳሌ ሆና መቅረቧን ገልጸዋል።

አፍሪካውያውን አካባቢን በሚበክል የኃይል አማራጭ ጥገኛ ከመሆን ይልቅ እንደ ኢትዮጵያ እምቅ የውሃ ሃብቶችን በመጠቀም ታዳሽ ኃይልን ለልማት ማዋል እንዳለባቸውም ናይጄሪያዊው ምሁር ተናግረዋል።

በላሉ ኢታላ

#EBC #ebcdotstream #GERD #resilence