የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የከተማችን ተጨማሪ ድምቀት በሆነው ከኡራኤል - ቦሌ መድኃኔዓለም እስከ ቦሌ ቪአይፒ (VIP) ተርሚናል የሚያገናኘውን የኮሪደር ልማት፣ ለአካባቢው ተጨማሪ ውበት የሚያጎናፅፉ እና ለሕዝብ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸውን ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች አካትተን አጠናቀናል ብለዋል።
ከንቲባዋ በመልዕክታቸው፣ ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ተጨማሪ ውበት ከማጎናጸፍ ባለፈ ለሕዝቡ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸውን ዘርፈ-ብዙ ስራዎች በውስጡ መያዙን አብራርተዋል።
ይህ መስመር ቀደም ሲል ደረጃቸውን ያልጠበቁ መንገዶች፣ የእግረኛና የሳይክል መንገድ እጥረት፣ እንዲሁም ከፍተኛ የመኪና ማቆሚያ ችግር የነበረበት መሆኑን ያስታወሱት ከንቲባዋ፤ ዛሬ ግን በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት አካባቢው ለዐይን ማራኪና ዘመናዊ መልክ መያዙን ገልጸዋል።
እንደ ከንቲባዋ ገለጻ፣ ቀደም ሲል ያልነበሩ የስፖርት ሜዳዎች፣ የሕፃናት መጫወቻዎችና የህንፃዎች ውበት አሁን በታላቅ ጥራት ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።
ፕሮጀክቱ በውስጡ የያዛቸውን ዋና ዋና የልማት ሥራዎች ከንቲባዋ እንደሚከተለው ዘርዝረዋል፦
• 5.3 ኪ.ሜ የአስፋልት መንገድ፦ 60 ሜትር ስፋት ያለውና በሁለቱም በኩል 4 መስመሮችን የያዘ፤
• የትራንስፖርት ተርሚናል፦ ዘመናዊ የታክሲና የአውቶቡስ ተርሚናሎች፤
• የእግረኛና የሳይክል መንገድ፦ 10.538 ኪ.ሜ የእግረኛ መንገድ (ከ5 እስከ 10 ሜትር ስፋት ያለው) እና 4 ኪ.ሜ የብስክሌት መስመር፤
• የመኪና ማቆሚያ፦ በመንግሥትና በግለሰቦች ትብብር በአንድ ጊዜ እስከ 2,000 መኪናዎችን (900 ከቤት ውጭ እና 1,100 በህንፃዎች ውስጥ) ማቆም የሚችሉ ስፍራዎች፤
• የኤሌክትሪክ ቻርጅ ጣቢያ፦ 3,442.38 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ፤
• የትራንስፖርት መቆሚያዎች፦ 15 የታክሲና አውቶቡስ ማቆሚያዎች፤
• የንግድና መዝናኛ ስፍራዎች፦ 8 ካፌዎች ከሕዝብ መጸዳጃ ጋር፣ ፕላዛዎች እና ለአነስተኛ ንግዶች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ሱቆች፤
• አረንጓዴ ልማት፦ 5 ፋውንቴኖችን ያካተቱ ውብ አረንጓዴ ስፍራዎች፤
• የስፖርት ማዘውተሪያዎች፦ የእግር ኳስና የቅርጫት ኳስ ሜዳዎች እንዲሁም የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎች፤
• የህንፃዎች ዕድሳት፦ ውበታቸው ተመልሶ የታደሱ ከ200 በላይ ሕንፃዎች ፣ በከፍተኛ ጥራትና ፍጥነት ተሰርተዋል።
•ደረጃውን የጠበቀ የፍሳሽ (Sewerage) እና የውሃ መውረጃ (Drainage) መስመር ያልነበረው፣ እንደ ሸረሪት ድር የተወሳሰቡ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም ገመዶች ያሉበት፣ እንዲሁም የደህንነት ካሜራዎች ያልተገጠሙለት የነበረ ሲሆን፤
አሁን ደረጃውን የጠበቀ የፍሳሽ እና የውኃ መውረጃ መስመር ዝርጋታ፣ እና ዘመናዊ መብራት እና የደህንነት ካሜራዎች ተገጥመውለታል።
እነዚህ አስደናቂ ተግባራት በሦስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መጠናቀቃቸው የታላቅ ደስታ ምንጭ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ "ይህ ፕሮጀክት የከተማችን ብቻ ሳይሆን የሀገራችን ኩራትና ገጽታን የሚቀይር ስኬት ነው" ብለዋል።
በ24/7 የሥራ ባሕል ቀንና ሌሊት ለደከሙ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሠራተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
እንዲሁም ላቅ ያለ ትብብር ላደረጉ ባለሀብቶች፣ ነጋዴዎችና የህንፃ ባለቤቶች ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።