Search

በድምፅ ማጉያ ከመስማት በሞባይል መተግበሪያ እስከመደመጥ በኢትዮጵያውያን እጆች ላይ የደረሰው የ90 ዓመቱ የበኩር ድምፅ

ዓርብ መስከረም 02, 2018 673

በኢትዮጵያ የአሁኑን የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ ለማቋቋም ስራ ሲጀመር ዘርፉ በአለም ላይ ገና ለጋ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የሬዲዮ ስርጭት ስትጀምር አሁን ላይ ስመጥር የሆኑ፤ ያኔ ግን ገና ያልተመሰረቱ ሀገራት ነበሩ፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ መላው አፍሪካ በቅኝ ግዛት እየማቀቀም ነበር፡፡

የብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ለዓለም ገና እንግዳ በነበረበት በዚያ ወቅት ታዲያ የኢትዮጵያ ሬዲዮ በአየሩ ላይ መናኘት ጀምሯል፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ስርጭት ሲጀምር እንደአሁኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጅ አልተስፋፋም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ስራውን ፈታኝ አድርጎት እንደነበር ይነገራል፡፡

በጅማሮው ወቅት ድምፅ በመቅዳት ወይም ሪከርድ በማድረግ አቀናብሮ ማስተላለፍ አይቻልም፡፡ ለሰዓት እወጃ ሳይቀር ደወል ስቱዲዮ ውስጥ በተዘጋጀ ሰው በአካል ይደወላል፤ ዜና እና ሙዚቃ በቀጥታ ይቀርባል፡፡ በወቅቱ የሬዲዮ መቀበያ መሳሪያው በብዙ ሰዎች ዘንድ ባለመኖሩ በትላልቅ ከተሞች ስርጭቱን በድምጽ ማጉያ አማካኝነት ነዋሪው ሰብሰብ ብሎ እንዲሰማ ይደረግም ነበር፡፡ አዲስ አበባ ላይ የአድማጭ አስተያየት ከመንገድ ላይ ሰው ተጠርቶ በቀጥታ ከስቱዲዮ ይደመጣል፡፡ ምክንያቱም ያኔ እንዳሁኑ ስራውን ሁሉ በቀላሉ ለማከናወን የሚያስችል ቁሳቁስ አልተሟላም፡፡

ይሁንና ሬዲዮ ጣቢያው ራሱን ቀስ በቀስ በቁሳቁስ እያደራጀ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቀጠናው ሀገራትም ጭምር ስርጭቱ ናኝቷል፡፡ በዓለም ዙሪያ የተሰሙ ወቅታዊ መረጃዎችን ዜና ፋይልን ጨምሮ በተለያዩ የዜና እወጃ መርሃግብሮቹ አማካኝነት አሁንም ድረስ በብዙ ኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ታትመው በሚገኙ ጋዜጠኞች ለህዝቡ አድርሷል፡፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍቡና ቡና የሚለውን መዝሙር በተከታታይ ከማስደመጥ ጀምሮ በርካታ ጥንቅሮችን እያዘጋጀ ለአድማጭ አድርሷል፡፡ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እና የመንግሥታት ለውጥን የተመለከቱ ዘገባዎች ተላልፈውበታል፡፡ ከዳሎል ዝቅታ እስከ ራስ ደጀን ከፍታ የኢትዮጵያን ታሪካዊ እና ሰው ሰራሽ ሃብቶች አስተዋውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሬዲዮ የሀገሪቱ የኪነ ጥበብ ዘርፍ አሁን ለደረሰበት ደረጃ አሻራው ከፍ ያለ ነው፡፡ በሙዚቃው በኩል አበርክቶው ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ኦርኬስትራ ምስረታ ይጀምራል፡፡ በርካታ ድምፃዊያን የሙዚቃ ስራዎቻቸውን በኢትዮጵያ ሬዲዮ ስቱዲዮ ቀርፀዋል፡፡ በዚህም የትም የማይገኙ ሙዚቃዎች ጭምር አሁን ላይ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የሙዚቃ ክምችት ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ሬዲዮ ጣቢያው የድምፅ ክምጭት (አርካይቭ) ሃብታም ነው፡፡

ሥነ - ፅሁፍን ከፍ አድርጎ የሰቀለው ፍቅር እስከ መቃብርን ጨምሮ የተለያዩ መጽሃፍት በኢትዮጵያ ሬዲዮ ተተርከው ለአድማጭ ደርሰዋል፡፡ በዚህም ሬዲዮ ጣቢያው ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የክፍለ ዘመኑ ጀግና የሚል እውቅና አግኝቷል፡፡ አድማጭን በስሜት ብድግ ቁጭ ያደረጉ የስፖርት መረጃዎች በኢትዮጵያ ሬዲዮ ተላልፈዋል፡፡ እሁድ እና ቅዳሜን የሚያስናፍቁ የመዝናኛ መሰናዶዎች ቀርበውበታል፡፡ ሬዲዮ ጣቢያው ያልዳሰሰው ርእሰ ጉዳይ የለም፡፡ በኢትዮጵያ አሁን ላይ ቁጥራቸው ለበዙት የሬዲዮ ጣቢያዎች እና በሙያው ከፍ ያለ ስም ለያዙት ጋዜጠኞች መነሻቸው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ነው፡፡

ሬዲዮ ጣቢያው አሁንም የይዘት እና አቀራረብ ለውጦችን እያደረገ ለኢትዮጵያዊያን የመረጃ ምንጭነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡

ብዙ ከፍታ እና ዝቅታዎችን ያለፈው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ታዲያ ስርጭት ከጀመረ ዛሬ መስከረም 2/2018 . 90 ዓመት ሞልቶታል፡፡ ይህ አንጋፋ የሬዲዮ ጣቢያ ታሪኩ ረጅም ነው፡፡ አመጣጡን በአጭሩ እንንገራችሁ፡-

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ ግንባታን የመሰረት ድንጋይ 1923 . በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ በሚባለው አካባቢ አስቀመጡ፡፡ በመሰረት ድንጋዩ ላይ የሰፈረው ፅሁፍም "ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ በነገሡ በሁለተኛው ዓመት ኢትዮጵያን ከዓለም መንግሥታት ጋር የሚያገናኝ ያለ ሽቦ ቃል የሚያሳልፍ መኪና የሚቆምበት ቤት ሲመሰረት በሀምሌ 14 ቀን 1923 . የመጀመሪያውን የማዕዘን ድንጋይ አኖሩ" ይላል፡፡ ግንባታው በታህሳስ ወር 1927 . ተጠናቆ በቀጣይ ዓመት አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ ይሄውም መስከረም 2/1928 . ነበር፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ "ይህ የምትሰሙት ድምፅ የእኔ የንጉሣችሁ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ነው" በማለት የመጀመሪያውን መልዕክት በሬዲዮ ጣቢያው አሰሙ፡፡

በአዲስ አበባ አሁን ላይ ንፋስ ስልክ የሚባለው አካባቢ ስያሜውን ይዞ የቀረው የሬዲዮ ጣቢያው ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ላይ ከሰፈረው "ያለ ሽቦ ቃል የሚያሳልፍ መኪና" ከሚለው ፅሁፍ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ይሁንና የነፋስ ስልክ ሬዲዮ ጣቢያ ብዙ ሳይቆይ በአመቱ አዲስ አበባን በተቆጣጠረው የፋሽስት ጣሊያን ወራሪ ሃይል አገልግሎቱ ተቋረጠ፡፡ ይኸው ሃይል የነፋስ ስልኩን ጣቢያ በማስቀረትና የራሱን ሬዲዮ ጣቢያ አቡነ ጴጥሮስ አደባባይ አካባቢ በማቋቋም ወረራውን ለማሳካት በሚያስችለው መልኩ ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨቱን ቀጠለበት፡፡መጠሪያውንም የኢጣሊያ የምስራቅ አፍሪካ ሬዲዮ ጣቢያ ብሎ ሰየመው፡፡

ፋሽስት ጣሊያን 5 አመታት በኋላ 1933 . በሽንፈት ሀገር ለቆ ሲወጣ ታዲያ ይኸንኑ ሬዲዮ ጣቢያ አፈራርሶት ነበር፡፡ ይሁንና 1934 . ጣቢያው ጥገና ተደርጎለት በአማርኛ፤ በሶማሊኛ፤ በእንግሊዝኛና በአረብኛ ቋንቋዎች ዜና፤ አስተያየት እና ሙዚቃ እንደገና ማቅርብ ስለመጀመሩ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ባሳተመው መጽሄት ላይ የተቀመጠው መረጃ ያመለክታል፡፡ በወቅቱ እነ ከበደ ሚካኤል፤ እነ አምደሚካኤል ደሳለኝና ሌሎችም በጋዜጠኝነት ስራው ተመድበው ዝግጅቶችን ያቀርቡ ነበር፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም በወቅቱ ሬዲዮ ጣቢያው ከወራሪው የጣሊያን ሃይል እጅ መውጣቱንና በአዲስ መልክ ወደ ስራ መግባቱን በማስመልከት "በግፍ የፋሽስቶች አፍ የነበረውን ሬዲዮ እንደገና ለህዝባችን እናገለግልበት ዘንድ እንሆ የብርሃንና ሰላም ዘመን ሆኗል" የሚል መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡

ከጣሊያን ወረራ ማብቃት በኋላ እንደገና ወደ ስራ የገባው ሬዲዮ ጣቢያው የኢትዮጵያ ህዝብ ሬዲዮ ጣቢያ ተብሎ ተሰየመ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱን የሚያወድሱ፤ 5 ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት የነበረውን የአርበኝነት ገድል የሚያወድሱና የሚያመሰግኑ፤ ፕሮግራሞችም በብዛት ተላለፉ፡፡ ከዜና፤ ከትምህርታዊ ፕሮግራሞችና ከመዝናኛ ዝግጅቶች ባሻገር የንግድና የመንግሥት ማስታወቂያዎችም የስርጭቱ አካል ሆኑ፡፡

1942 . ማስታወቂያ ሚኒስቴር የጣቢያውን ፕሮግራም በበላይነት እንዲቆጣጠር ኃላፊነት ተሰጠው፡፡ ይህ ከሆነ 5 ዓመታት በኋላ ደግሞ የተደራጀ ነበር የተባለለት የስቱዲዮ መሳሪያ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ግቢ ውስጥ ተተከለ፡፡ ሌሎች መሳሪያዎችም በአስመራ፣ በጎንደር፣ በበደሴ፣ በደብረማርቆስ፣ በድሬዳዋ፣ በሀረር፣ በጂማ፣ በነቀምት፣ በአሰላ፣ በይርጋለም እንዲሁም በመቐለ እንዲተከሉ ተደረገ፡፡በጌጃ ዴራ የተቋቋመው ባለ 100 ኪሎዋት ማስተላለፊያ ጣቢያም 1949 . ለሬዲዮ ጣቢያው አዲስ ጉልበት ሰጠው፡፡

1954 . ደግሞ አዲስ የድምፅ መቅረጫና ማሰራጫ መሳሪያዎችን በመጠቀም ለምዕራብ አፍሪካና ለምዕራብ አውሮፓ በእንግሊዝኛና በፈረንሳይኛ፤ ለምስራቅና መካከለኛው እሰያ እንዲሁም ለሰሜን አፍሪካ በአረብኛ፤ ለመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ በስዋህሊ ቋንቋዎች ፕሮግራሞችን ማስተላለፍ ጀመረ፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 35 የዘውድ በዓላቸውን በጥቅምት ወር 1959 . ሲያከብሩ መርቀው የከፈቱት ከፍተኛ አቅም የነበረው የሚዲየም ዌቭ ማሰራጫ ጣቢያም የሬዲዮ የስርጭት አድማስን አሰፋው፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የኢትጵያ ሬዲዮ ተብሎ እንደተጠራ ይነገራል፡፡ ጣቢያው እንዲህ አንዲያ እያለ 7 አመታት በኋላ ደግሞ ሌላ ታሪክ ውስጥ ገባ፡፡

ደርግ መንበረ ስልጣኑን ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለመውረስ ያዘጋጀውን መግለጫ በተለያ የሀገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎች አስተርጉሞ በመስከረም ወር 1967 . በኢትጵያ ሬዲዮ አንዲተላለፍ አደረገ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮም የሬዲዮ ጣቢያው ስያሜ ከኢትጵያ ሬዲዮ ወደ አብታዊት ኢትዮጵያ ድምጽ ተቀየረ፡፡ በወቅቱ ህዝቡን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለመቀስቀስ፤ ለማንቃት፤ እና ለማደራጀት የሚያግዙ የዘመቻ፣ የፉከራና የማርሽ ድምጾች በብዛት ይስተጋቡ ነበር፡፡

17 ዓመታት በዘለቀው የደርግ ስርዓተ መንግሥት ወቅት የሬዲዮ ጣቢያስን አብዛኛውን የአየር ሰዓት የሚሸፍኑት የአማርኛ መሰናዶዎች ሲሆኑ የእሁድ ፕሮግራም፤ እርስዎም ይሞክሩት፤ ግብርና፤ ኢኮኖሚ፤ ማኅበራዊ ኑሮ፤ ኪነ ጥበባት፤ የመፅሃፍት ዓለም፤ ስፖርት፡ ጤና፤ ወጣቶች፤ ቅዳሜ መዝናኛ፤ ሕግና ኅብረተሰብ፡ ደብዳቤዎች፤ የልጆች ዓለም፤ የሳይንስ ማህበርና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ሬዲዮ ጣቢያው እንደ አሜሪካ ድምጽ ቪኦኤ እና የጀርመን ድምጽ ዶቸቨሌ ያሉ ጣቢያዎች ከውጭ ለኢትዮጵያውያን ብለው በአገር ቤት ቋንቋ ያስተላልፏቸው የነበሩ አፍራሽ የሚል ስም የተሰጣቸውን መልእክቶች የሚመክት መረጃ የማቅረብ ኃላፊነት ተጥሎበትም ነበር፡፡

ከደርግ መንግሥት መውረድ በኋላ ሬዲዮ ጣቢያው እንደገና የኢትዮጵያ ሬዲዮ ተብሎ በተለይም 1980ዎቹ እና 90ዎቹ መላ ሀገሪቱን በሚያዳርስ ስርጭት ዝግጅቶችን በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎች ለአድማጭ አድርሷል፡፡

ሬዲዮ ጣቢያው በኢህአዴግ ዘመን መጨረሻ ብሄራዊ ሬዲዮ በሚል እንዲጠራ ተደርጎ የነበረ ሲሆን በለውጡ ሰሞን የኢትዮጵያ ሬዲዮ ወደሚለው ስያሜው እንዲመለስና ተቀይረው የነበሩ ተወዳጅ ፕሮግራሞችም እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡

90 ዓመታትን ለተሻገረ ጊዜ ብዙ ከፍታና ዝቅታን ያሳለፈው የኢትዮጵያ ሬዲዮ አሁን ላይም ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጅ በመጠቀም ኢትዮጵያን እያገለገለ ይገኛል፡፡ አማርኛ፤ አፋን ኦሮሞ፤ ትግርኛ፤ አፋርኛ እና ሶማሊኛ አሁን ላይ በጣቢያው እየተላለፉ የሚገኙ ቋንቋዎች ናቸው፡፡

 

 

በብርሃኑ አለሙ