የቀድሞው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ቲቦር ናዢ የሕዳሴ ግድብ ከአጋር ሀገሮች እርዳታ ይልቅ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ብቻ መገንባቱ ከሌሎች ግድቦች በተለየ ልዩ ግድብ ያደርገዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ቲቦር ናዢ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ "ከሲ.ኤን.ኤን" ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ይህ ግድብ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ አቅርቦት በእጥፍ የሚጨምር በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ታላቅ ስኬት የተቀዳጁበት ፕሮጀክት ነው ሲሉም ገልፀዋል።
ዲፕሎማቱ አክለውም፤ ግብፅ ለዓባይ ወንዝ አንዲት ጠብታ ውኃ ሳታዋጣ በታሪክ ግን በወንዙ ጉዳይ ላይ ለመወሰን ሁሉንም ስፍራ ይዛ መቆየቷን አንስተዋል።
ያ የተዛነፈ የኃይል ሚዛን አሁን ተቀይሯል ያሉት አምባሳደሩ፤ የቆዩ ውሎች በዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (ሲ. ኤፍ. ኤ) መተካታቸውን ጠቅሰዋል።
ግብፅ እና ሱዳን ይህን አዲስ ፍትሃዊ አሰራር በመቃወም ፊርማቸውን አለማኖራቸውን አስታውሰው፤ አብዛኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ግን የትብብር ማዕቀፉ ላይ መስማማታቸውን ገልፀዋል።
በዚህ ምክንያት የቀድሞዎቹ ስምምነቶች በተመሳሳይ መንገድ ተፈጻሚነት ያጡ ሲሆን፣ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ ያለው የኃይል ሚዛን በመሠረቱ ወደ ፍትሃዊነት ተቀይሯል ብለዋል ቲቦር ናዢ።
በሴራን ታደሰ