የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የኒው ዮርክ ስምምነትን የሚደግፍ የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምፅ ማፅደቁን አናዶሉ ዘግቧል።
የኒው ዮርክ ስምምነት ለፍልስጤም እውቅና ለመስጠት እንዲሁም ለእስራኤል-ፍልስጤም ግጭት የሁለት ሀገርነት መፍትሔን ለማስቀጠል ያለመ ነው።
“የፍልስጤምን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ እና የሁለት ሀገርነት መፍትሔን ለመተግበር” በሚል የተዘጋጀው የውሳኔ ሃሳብ በ142 ድጋፍ፣ በ10 ተቃውሞ እና በ12 ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።
የውሳኔ ሃሳቡን ከተቃወሙት መካከል እስራኤል እና አሜሪካ የሚገኙበት ሲሆን፤ በተመድ የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን ይህን ስምምነት ተብዬ ማፅደቅ ሰላም ለመፍጠር ቁርጠኝነት አለመኖሩን ያሳያል ብለዋል።
የአሜሪካው ተወካይ ሞርጋን ኦርታጉስ በበኩላቸው፥ ስምምነቱ ግጭቱን ለማስቆም የሚደረጉ ሁነኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን የሚያስተጓጉል ነው ብለዋል።
አክለውም ስምምነቱ ለሀማስ የልብ ልብ የሚሰጥ እና የሰላም ዕድልን የሚጎዳ ነው ብለዋል።
በፈረንሳይ እና በሳውዲ አረቢያ የቀረበውን የኒው ዮርክ ስምምነት ባለፈው ሐምሌ ወር በተመድ ዋና መሥሪያ ቤት ስብሰባ በተካሄደበት ወቅት 17 ሀገራት ፈርመውት እንደነበር ዘገባው አስታውሷል።
በነስሩ ጀማል
#EBCdotstream #UN #GeneralAssembly #Israel #Palestine #NewYorkDeclaration