ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለአፍሪካውያን ጭምር ኩራት መሆኑን የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች ገለጹ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚጠቀሱ 10 ታላላቅ ግድቦች አንዱ የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ በራስ አቅም መገንባቱም በአህጉሪቱ ትልቅ መነሳሳትን የፈጠረ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በኢንቴቤ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ (ኡጋንዳ) የበረራ ተቆጣጣሪ የሆኑት ዛም ዛም፥ ግድቡ ያለ አንዳች የውጭ ድጋፍ መገንባቱ የሚያኮራ ነው ብለዋል።
ዛም ዛም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ግድቡ ቀጣናዊ ትስስርን በማሳለጥ ረገድ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸው፤ የኃይል አቅርቦቱ በቀጣናው ያለውን የኢንዱስትሪ ልማት እንደሚያፋጥነው አክለዋል።
በኬንያ የአካባቢ፣ አየር ንብረት ለውጥ እና ደን ልማት ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ምክትል ዳይሬክተር ሚካኤል ኦኩሙ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ግዙፍ እና አስደናቂ ግድብ መገንባቱ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካውያን ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
#Ethiopia #GERD #Inauguration