ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተባበረ የኢትዮጵያውያን ክንድ የተገነባ ታላቅ ፕሮጀክት ነው፤ በዚህ ፕሮጀክት ዐሻራውን ያላሳረፈ ኢትዮጵያዊም ሆነ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የለም።
ተማሪዎች፣ ወጣቶች፣ እናቶች፣ አባቶች፣ ሠራተኞች፣ ተቋማት … ሁሉም በሕዳሴ ግድብ ላይ ዐሻራቸውን አሳርፈዋል።
የኖክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ጥላሁን ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ተቋሙ ባለፉት 14 ዓመታት ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ በተለያየ መንገድ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ተቋሙ ለግድቡ ግንባታ የሚያገለግል ነዳጅ ማከማቻ ሠርቶ ከማስረከቡ በተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ስለማድረጉም ነው አቶ ታደሰ የተናገሩት።
ሕዳሴ ግድብን ኢትዮጵያውያን ያለአንዳች ልዩነት በትብብር ለስኬት አብቅተነዋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የታየውን ሕዝባዊ ርብርብ ታሪክ በደማቁ የሚዘክረው ስለመሆኑ ነው የገለጹት።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያውያን በተንኮል እና በሴራ፣ በዘር እና በፖለቲካ የምንከፋፈልበትን ሁኔታ ወደ ጎን ትተን በአንድነት እና በኅብረት በመሥራት የማይታሰብ የሚመስለውን የቻልንበት ዳግማዊ ዓድዋችን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ያለማንም ድጋፍ እና እርዳታ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ እውን በማድረግ ዜጎችን ከጭለማ ወደ ብርሃን ከማሸጋገር ባለፈ ለሀገራዊ ብልፅግና ትልቅ መሠረት ጥለናል፤ ይህ ስኬት ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በተመሳሳይ መንገድ ለመከወን ስንቅ የሚሆነን ነው ብለዋል።
ሰላማችን ከተረጋገጠ ብልፅግናችን አይቀሬ ነው ያሉት አቶ ታደሰ፤ ሰላምን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ሁሉም የድርሻውን ማበርከት እንዳለበት አመላክተዋል።
በሜሮን ንብረት
#Ethiopia #GERD #Inauguration