Search

የትምህርት ቤት ምገባ:- የኢትዮጵያ ስኬት ለዓለም አርአያነት!

ቅዳሜ መስከረም 03, 2018 629

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ይፋ ያደረገው “የዓለም አቀፍ የትምህርት ቤት ምግብ ሁኔታ” የተባለ ሪፖርት፣ በትምህርት ቤት የምግብ ፕሮግራሞች ሽፋን ላይ ታይቶ የማያውቅ ዕድገት መመዝገቡን ገልጿል። 

 

ይህ እመርታ ለልማት ዓለም ያልተለመደ መልካም ዜና ሲሆን፣ ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት ተላቆ በብሔራዊ መንግሥታት አመራር የሚመራ ፖሊሲ ሆኖ መውጣቱን ያሳያል።

 

ሪፖርቱ በግልጽ እንደሚያሳየው፣ ይህ ስኬት የተገኘው በየአገራቱ መንግሥታት የፕሮግራሙን የልማት ኃይል በመረዳት እና ብሔራዊ በጀታቸውን በእጥፍ በማሳደግ ነው። 

 

ይህ ቁርጠኝነት፣ ትምህርት ቤት ምግብ ለሕፃናት ደኅንነት ብቻ ሳይሆን፣ ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚሰጠውን ሁለገብ ጥቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው።

 

አዲስ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የትምህርት ቤት የምግብ ፕሮግራሞች የሕፃናትን በትምህርት ቤት መመዝገብ እና ትምህርታቸውን አለማቋረጥ ብቻ ሳይሆን፣ የመማር እና የማሰብ ችሎታቸውንም ከፍ ያደርጋሉ። 

 

ይህ ደግሞ በዛሬው ጊዜ የሚታየውን “የትምህርት ቀውስ” ለመፍታት ውጤታማ መንገድ መሆኑን ያመለክታል። በሪፖርቱ ላይ እንደተጠቀሰው፣ ለእያንዳንዱ 1 ዶላር የሚደረግ ኢንቨስትመንት ከ7 እስከ 35 ዶላር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያስገኛል።

 

ፕሮግራሞቹ 466 ሚሊዮን ሕፃናትን ተጠቃሚ ሲያደርጉ ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ7.4 ሚሊዮን የምግብ አብሳይ ስራዎችን ፈጥረዋል። 

 

በተጨማሪም፣ “ከአካባቢው ምርት የተዘጋጀ የትምህርት ቤት ምግብ” (Home-Grown School Feeding) የሚባሉት ሞዴሎች የአካባቢውን የግብርና ምርት በማነቃቃት፣ ለአነስተኛ አርሶ አደሮች የገበያ ዋስትና በመስጠት እና ለአካባቢው ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

 

ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፣ ፕሮግራሞቹ ለሴቶች እና ለልጃገረዶች ልዩ ጥቅም ይሰጣሉ። ልጃገረዶች በትምህርት እና በጤና ረገድ ከወንዶች የበለጠ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ ሴቶች ደግሞ በምግብ አቅርቦት ሰንሰለት እና በሌሎች የአካባቢው ስራዎች በመሳተፍ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው እንዲያድግ ይረዳል።

 

ሪፖርቱ አፍሪካ በዚህ የዕድገት ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም መሆኗን አጉልቶ ያሳያል። በተለይም በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በማዳጋስካር እና በሩዋንዳ የተመዘገበው መሻሻል ተስፋ ሰጪ ነው። 

 

ይህ የሚያሳየው የአፍሪካ መንግሥታት የሕፃናትን ደኅንነት እና ትምህርት ከሁሉም በላይ ቅድሚያ መስጠታቸውን ነው። 

 

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ በፕሮግራሙ ዕድገት ግንባር ቀደም ከሆኑ አገራት አንዷ ናት። በርካታ ሚሊዮን ህጻናት የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ ናቸው። 

 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደ ጥሩ ተሞክሮ ተጀምሮ ወደ ሌሎች ክልሎች የተስፋፋው የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም፣ በተማሪዎች የመማር ተሳትፎ፣ በትምህርት ቤት መቅረት መቀነስ እና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከመቀነስ ባለፈ፣ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እና የአካባቢ ኢኮኖሚን ለማነቃቃት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

 

ምንም እንኳን ይህ ታላቅ ስኬት ቢመዘገብም፣ ሪፖርቱ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች ላይ ሊደርስ ስለሚችለው አደጋ ያስጠነቅቃል። 

 

እነዚህ ሀገሮች የገንዘብ ምንጭ ውስን በመሆኑ፣ ለትምህርት ቤት ምግብ ፕሮግራሞች የውጭ እርዳታ አሁንም ወሳኝ ነው። ሆኖም፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድጋፍ አቅጣጫ እየተቀየረ እና የሀገር ውስጥ በጀቶች ለብቻቸው ፍላጎቱን ለማሟላት አቅም እያጠሩ መሆኑ የፕሮግራሞቹን ቀጣይነት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። 

 

ስለዚህ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም የትምህርት ቤት የምግብ ጥምረት አባል የሆኑ ሀገራት፣ በእነዚህ ሀገሮች ላይ ትኩረት አድርገው ድጋፋቸውን መቀጠል አለባቸው።

 

የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ሪፖርት፣ የትምህርት ቤት የምግብ ፕሮግራሞች ከቀላል የሰብዓዊ እርዳታነት ወደ ውጤታማ የልማት ፖሊሲ መሸጋገራቸውን አረጋግጧል። ይህ ዕድገት የተገኘው በመንግሥታት ቁርጠኝነት፣ በወሳኝ የገንዘብ ኢንቨስትመንት እና የፕሮግራሙን ሰፊ ጥቅም በማመን ነው። 

 

የኢትዮጵያ እና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ያሳዩት አመራር ለሌሎችም አርአያነት ያለው ሲሆን፣ ይህ ስኬት ከቀጠለ በሚቀጥሉት ዓመታት የበርካታ ሚሊዮን ሕፃናትን ሕይወት እና የሀገራትን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመለወጥ የሚቻል ይሆናል።

 

በሰለሞን ገዳ