የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቀጣናው የኢኒርጂ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚፈጥር የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ዋና ፀሐፊ ቺሌሼ ካፓፑዌ ገለጹ።
ዋና ፀሐፊዋ የሕዳሴ ግድብ ቀጣናዊ የኢነርጂ ትስስርን ለማጠናከር እና የኃይል አቅርቦትን በማሳደግ ረገድ ጉልህ አበርክቶ እንዳለው አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢነርጂ ያላትን ቁርጠኝነት እና የውሃ (ሃይድሮ) ኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ አቅሟን ለመጠቀም እያደረቻቸው ያሉ ጥረቶችን ዋና ፀሐፊዋ አድንቀዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን በቀጣናው የኢኒርጂ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ ኢንቨስትመንት መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ረገድም የጎረቤት ሀገራት የሚያጋጥማቸውን የኃይል እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስም ለኢዜአ ገልጸዋል።

እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች ቀጣናዊ ትብብርን በማጠናከር እና የጋራ የኢነርጂ አቅርቦት እና ደህንነትን ያሻሽላል ነው ያሉት ዋና ፀሐፊዋ።
በምስራቅ እና ደቡባዊ የአፍሪካ ቀጣና ካሉ ዋንኛ ጉዳዮች አንዱ የኢኒርጂ እጥረት መሆኑን ቺሌሼ ካፓፑዌ አንስተዋል።
በቂ የኃይል አቅርቦት አለመኖሩ የኢንዱስትሪ እድገቱን እየጎተተ እንደሚገኝ እና የእሴት መጨመር ውስንነት መፍጠሩን አመልክተዋል።
ይህም በኮሜሳ አባል ሀገራት የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ነው የተናገሩት።
አባል ሀገራቱ የኢኒርጂ አቅርቦታቸውን ለማሳደግ የተቀናጀ አሰራር ሊከተሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኮሜሳ ከአጋሮች ጋር በመሆን የኢነርጂ ክፍተቱን ለመሙላት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በቀጣናው የኤሌክትሪክ ሽፋን እና ተደራሽነት ለማሳደግ ከዓለም ባንክ ጋር እያከናወነ ያለው የአጋርነት ሥራ ለአብነት ጠቅሰዋል።