በአዲስ አበባ ለሚሠሩት እና ለተሠሩት ሥራዎች ሕዝቡ በመደገፍ ከጎናችን ሆኗል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ የከተማዋ ዕድገት ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ ስለመሆኑ ገልጸው፣ አዲስ አበባን ለማስዋብ እና ምቹ በማድረግ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናችን አልተለየም ብለዋል።
አንዳንድ ሰዎች ዓላማውን ካለመረዳት የተለያዩ ሐሳቦችን ቢያነሱም ሥራውን ሲረዱት ግን ደግፈውናል ሲሉም ተናግረዋል።
በልማቱ ዙሪያ የተሳሳቱ መረጃዎች ቢንሸራሽሩም ዓላማው ንፁህ፣ የተሻሉ መኖሪያ ቤቶች እና የተሻለ መሰረተ ልማት ለከተማዋ መገንባት እንደሆነ በተግባር አሳይተናል ነው ያሉት።
የተሠሩትም ልማቶች በርካቶች የሚደሰቱበት እና የሚኮሩበት እንደሆነ ገልጸዋል።

"በካዛንችስ፣ በወንዞች ዳርቻ ልማት እንዲሁም በሌሎች የልማት ሥራዎች ምክንያት ከሰፈራቸው ያስነሣናቸው ሰዎች በርካታ ቢሆኑም ዓላማው ለበጎ መሆኑን በመገንዘብ ሕዝቡ አልተቃወማቸውም" ነው ያሉት ከንቲባዋ።
"ሕዝቡ በሚገባ የተሻለ ነገር እንዳገኘ አፉን ሞልቶ ይናገራል፤ እኛ ደግሞ ትኩረታችን ለመረጠን ሕዝብ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።
ከተማዋ ለነዋሪዎች የምትመች ከማድረግ ጎን ለጎንም ለቱሪስት ፍሰት ተመራጭ እየሆነች ስለመምጣቷም አንሥተዋል።
ከተማዋን መልሶ በመገንባት ሂደት ውስጥ የነበሩ ተግዳሮቶች እንዳሉ የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች፣ በግንባታው ወቅት የትራፊክ እንቅስቃሴን ላለማወክ ምሽት እና ሌሊት ጭምር በመሥራት የሥራ ባህሉን መቀየር ተችሏል ብለዋል።
እንደሌሎቹ ሀገራት ከተማዎች ምርጥ ከተማ አለችኝ ለማለት የሚያስችል ምርጥ ሥራዎች ሠርተናል ሲሉም ተናግረዋል።
በሜሮን ንብረት