Search

የሞተር ጀልባዎች ከቀረጥና ከታክስ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

ቅዳሜ መስከረም 03, 2018 72

በሞተር ኃይል የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ከቀረጥ እና ከታክስ ነፃ ሆነው እንዲገቡ መፈቀዱን  የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚነስቴሩ በላከው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ቱሪዝምን በመሳብ ረገድ ሊያገለግሉ የሚችሉ ከ20 በላይ ታላላቅ ሐይቆች መኖራቸውን አመላክቷል።

ሐይቆቹ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ሲባል የገንዘብ ሚኒስቴር በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 (እንደተሻሻለ) አንቀጽ 129 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች በሞተር ኃይል የሚሠሩ የተለያዩ ዓይነት ጀልባዎችን ለአንድ ዓመት ያህል ከማናቸውም ቀረጥ እና ታክስ ነፃ ሆነው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያስገቡ የሚያስችል መመሪያ አውጥቷል።

በዚህም መሠረት መመሪያው ከወጣበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ማናቸውም በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራ ሰው የሚከተሉት ጀልባዎች ወደ ሀገር ማስገባት እንደሚችል ሚኒስቴሩ አስታውቋል። 

1. ፈጣን እና ቅይጥ አገልግሎት የሚሰጡ ለዓሣ ማጥመጃ እና ለአጫጭር ርቀት የመንገደኛ ማጓጓዣ ወዘተ. የሚውሉ አነስተኛ እና መካከለኛ የሞተር ጀልባዎች(outboard motor boats)

2. በመካከለኛ ሐይቆች ላይ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ፤ ለቱሪስት እና ለአደጋ ጊዜ የሚያገለግሉ ፈጣን ጀልባዎች(speedboats)

3. ለቱሪስቶች ጉብኝት አገልግሎት የሚውሉ ግልጽ ወይም በከፊል የተሸፈኑ  ጀልባዎች(Tourist excursion boats)

4. ለሰዎች ማጓጓዣ የሚውሉ ጀልባዎች (Ferries)

5. ለጥናት እና ምርምር የሚያገለግሎ ጀልባዎች(Research boats)

6. ለግል አገልግሎት የሚውሉ ጀልባዎች (Private motor boats)

7. በጸሐይ ኃይል እና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ጀልባዎች( Eco boats)

8. ጠፍጣፋ እና ባለ ጣሪያ የሞተር ጀልባዎች (pontoon boats)

እና የመሳሰሉት ለሀገራችን ሐይቆች ተስማሚ የሆኑ የሞተር ጀልባዎች ቀረጥ እና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር ሊገቡ ይችላሉ ሲል የገንዘብ ሚኒስቴር ገልጿል።