ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ አጠናቃ ማስመረቋ አህጉራዊ መነሳሳት የሚፈጥር መሆኑን የአለም አቀፉ የንግድ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የአፍሪካ ቀጣናዊ ድርጅት ገለፀ፡፡
የአለም አቀፉ የንግድ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የአፍሪካ ቀጣናዊ ድርጅት ዛሬ ባወጣው መገለጫ የአፍሪካ ትልቁ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በመመረቁ ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ሲል መልእክቱን አስተላልፏል።
ድርጅቱ በመግለጫው፤ የህዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ድል ብቻ ሳይሆን፤ አህጉራዊ መነሳሳት የሚፈጥር ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ ስኬት አፍሪካ ያላትን የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብቷን ለመጠቀም ያላትን አቅም እንደሚያሳይም ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በግድቡ አማካኝነት የምታመነጨው ንፁህ ኢነርጂ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ከማስፋፋት ባለፈ አህጉሪቱ በቁርጠኝነት እየሰራችበት ላለው የአየር ንብረት ጉዳይ ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክትም ነው ድርጅቱ የጠቀሰው፡፡
ኢትዮጵያ በነዳጅ ላይ ጥገኛነትን በመቀነስ እና ዘላቂ እንዲሁም ታዳሽ የኃይል አቅርቦትን በማስፋት ልማትን ማረጋገጥ እንደሚቻል በተግባር አሳይታለች ብሏል መግለጫው፡፡
ይህ የኢትዮጵያ ስኬት ሌሎችን እንደሚያበረታታ ተስፋ እናደርጋለን ያለው ድርጅቱ፤ የአፍሪካ ሀገራት የኢነርጂ ሉዓላዊነት ላይ የሚያደርጉትን ጥረት ለማፋጠን እንደሚያግዝም ጠቅሷል።