የሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ የተመሰረተችበትን 878ኛ ዓመት እያከበረች ትገኛለች፡፡
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በስነ ስርዓቱ ላይ በክሬምሊን አቅራቢያ በሚገኘው የዛሪያዲዬ ፓርክ የሙዚቃ አዳራሽ ባደረጉት ንግግር፣ ሞስኮ በምድር ላይ ካሉ ምርጥ ከተሞች አንዷ ናት ሲሉ ተናግረዋል።
ሞስኮ በዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ከተሞች ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ የከተማዋን ታሪካዊ ሚና እና ለሠራዊቱ ያላትን ጠንካራ ድጋፍ አመስግነዋል።
ፕሬዝደንቱ ዋና ከተማዋ በዩክሬን ግጭት ወቅት ለሩሲያ ሠራዊት ጠንካራ የኋላ ደጀን ነበረች ሲሉም አሞካሽተዋል።
በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ወቅት ሞስኮ ከሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ጋር በኪዬቭ ድሮኖች በተደጋጋሚ ኢላማ እየተደረገች የምትገኝ ሲሆን፤ እነዚህ ጥቃቶች ብዙ ጊዜ የመኖሪያ ሕንፃዎችን እና የሲቪል መሰረተ ልማቶችን ያነጣጠሩ ናቸው።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በከተማዋ 878ኛ የልደት በዓል ላይ ባጋራው የቪዲዮ መልእክት፤ “እኛ ዲፕሎማቶች የዓለምን ከተሞች በሙሉ ጎብኝተናል፣ በፍፁም እርግጠኝነትም እንደ ሞስኮ ያለ ከተማ የለም ማለት እንችላለን” ሲል መግለፁን ስፑቲንክ ዘግቧል።
በሰለሞን ገዳ
#ebc #ebcdotstream #Russia Moscow