የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ታየ አፅቀ ሥላሴ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን የሚጠራጠሩትን ሁሉ ገርቶ፣ ነቃፊዎቻችንን አርሞ፣ አጉራህ ጠናኝ ያሉትን አስተካክሎ፣ አውርቶ አደሮችን በግዝፈቱ ገርምሟል ሲሉ ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ታየ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ በአዲስ አበባ በተደረገው ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ "ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ‘ተመፅዋች እና ተለቃሽ’ የሚለውን የመዛበቻ ቅፅል ስም አሽቀንጥሮ የጣለበት የእንችላለን ማሳያ ነው" ብለዋል።
የሕዳሴ ቁምነገር የዕድገት ግስጋሴ ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል የማይታሰብ መሆኑን አሳይቷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ኃይል ማመንጨት የፍትህ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የዕድገት መሰላል መሆኑን ገልፀዋል።
ሕዳሴ ግድብ ትናንት የነበረውን የኢትዮጵያውያንን የመንፈስ ጥንካሬ የሚያረጋግጥ፣ ዛሬ ያለንን ጥበብ እና ብልሃት የሚቃኝ እና ነገ የሚኖረንን የብርሃን ቀንዲል የሚያሳይ ታላቅ ገድል ነው በማለት ተናግረዋል።
"የሕዳሴ ሃሳብ በዓለም አደባባይ ሀቅን ፍለጋ የተከራከርንበት ሃሳብ በመሆኑ፤ ግድቡም የኢትዮጵያ እናቶች የአግዙኝ እና የደግፉኝ የተማፅኖ ዕንባ ምላሽ ነው" ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
"በምጥ የተያዙ እናቶችን በወሳንሳ ተሸክመን ጭላንጭል ብርሃን ወዳላት ክሊኒክ ለማድረስ የሞት እና የሕይወት ጉዞን ማድረግ ከብዶን፣ የውኃ እንስራ አዝለው የሚሄዱ ሴቶችን ማየት ታክቶን፣ የእናቶችን የጎበጠ ወገብ ማቅናት አለብን ብለን ባሰማነው የፍትሕ ጥያቄ ልቦና ያላቸው ሁሉ ከጎናችን ቆመው ዛሬ ለእናቶች ብርሃን ሆነናል" ሲሉም ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለእህትማማች ሀገራት በጋራ የመሥራት ዕድልን የሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ወደፊትም በጋራ እውን የምናደርጋቸው አያሌ ፕሮጀክቶች ስለሚኖሩ ግድቡን መነሻ ምዕራፍ አድርገን አብረን እንሥራ በማለት ጥሪ አቅርበዋል።
በሴራን ታደሰ
#EBCdotstream #Ethiopia #GERD