Search

ሕዳሴ በኅብረት የመቻላችን ህያው ምስክር ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

እሑድ መስከረም 04, 2018 69

ጅረቶች፣ ምንጮች፣ ብዙ ገባር ወንዞች ተጋምደው የፈተሉት ዓባይ ወርቁን፣ አፈሩን ግንዱን፣ ውሃውን ይዞ ያለማንም ከልካይ ከመንጎድ ተቆጥቧል፤ በሀገር ልጅ የተባበረ ኅብረት ተገድቦ ለሀገር ጥቅም መዋል ጀምሯል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን የተባበረ የልማት ትጋት እና ቆራጥ ውሳኔ ተሳክቷል፤ የሀገራችንን የቁጭት ዘመን ዘግቶ የንጋት ጉዞዋን አብስሯል፤ ከብርሃን ምንጭነቱ ባሻገር የነገ ብልፅግና መዳረሻችንን ተልሟል ነው ያሉት።

ግድቡ በመሪዎቻችን በሳል ውሳኔ፣ በሕዝባችን ኅብረት፣ በፀጥታ ኃይሎቻችንና በፕሮጀክቱ ሠራተኞች ፅናትና መስዋዕትነት የተሳካ፣ በመደመር እሳቤ የተገነባ የአሸናፊነታችን የብርሃን ዓምድ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ዛሬ ማለዳ የአዲስ አበባ ህዝብ "በኅብረት ችለናል" በሚል በነቂስ ወጥቶ የድጋፍ ሰልፍ በማድረግ የጋራ ድሉን ማክበሩን ጠቅሰው፤ አዎ ኢትዮጵያ ፈተናን በፅናት ተቋቁማ ማሸነፍ፣ ችግርን ወደ ዕድልና ድል መቀየር ትችልበታለች ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሑፍ።

“ሀገራችን ትናንት ያልገጠማት ፈተና አልነበረም፤ በኅብረት በድል ተሻግራዋለች፤ ዛሬም በልጆቿ ላብና ደም ፀንታ፣ አትችልም የሚሏትን በሕዳሴ ግድብ ችላ አሳይታለች፤ ነገም በሕዝባችንና በመንግሥት ጠንካራ የተባበረ ክንድ ህልሞቿን ታሳካለች” ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ለልጆቿ፣ ለአፍሪካና ፍትሐዊ ልማትን ለሚሹ የዓለም ሕዝብ ሁሉ የብርሃን፣ የብልፅግና እና የልዕልና ተምሳሌት ሆና ትቀጥላለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትናንትም ዛሬም ነገም ለሀገሪቱ ክብርና ዕድገት በአይበገሬነት እያሳየው ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።

#EBCdotstream #Ethiopia #GERD