Search

"በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የጋራ ጥቅምም ለማስከበር በትብብር መሥራት ይገባል" - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

እሑድ መስከረም 04, 2018 92

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ከኬኒያ የቱርካና አታከር ክልል አስተዳዳሪ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በቱርሚ ከተማ ተወያይተዋል።

በወሰን በሚገናኙ ሁለቱ አካባቢዎች መካከል ለዓመታት የዘለቀ መልካም የህዝብ ለሕዝብ እና የንግድ ግንኙነት መኖሩን ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ ግዙፉን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ አስመርቀው አዲሱን ዓመት በተቀበሉበት ማግስት የሚካሄድ ውይይት መሆኑ መርሐ-ግብሩን ለየት እንደሚያደርገው ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

ውይይቱ እንደ አንድ ቤተሰብ በሆኑ ሁለቱ ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ላይ እንደሚመክር ገልጸው፣ በዳሰነች እና በቱርካና ሕዝቦች መካከል ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሠላማዊ እና ያለውን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል እንዲሆን በቅንጅት እንደሚሠራ ተናግረዋል።

የቱርካና አታካር ክልል ልዩ የሠላም መልዕክተኛ ጆን ሙንየስ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ እና በኬንያ መካከል ከአጼ ኃይለ ሥላሴ እና ጆሞ ኬንያታ ጊዜ ጀምሮ የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነት እንዳለ አውስተው፤ ሕዳሴ ግድብ በመመረቁ እና ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት በሠላም በመቀበላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዳሰነች ቱርካና ኮሪደር ሁለቱን ህዝቦች ሊጠቅም የሚችል ፀጋ ያለበት ቀጣና መሆኑን አንስተው፣ አልፎ አልፎ ግን የህዝቦቹን የጋራ ጥቅም የሚጎዱ ግጭቶች ስለሚስተዋሉ ችግሩን ለመፍታት በአመራር ደረጃ ቁርጠኛ አቋም በመያዝ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በጋራ ውይይቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የኬንያ ፓርላማ አባላት እና የአታከር ክልል ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

በተመስገን ተስፋዬ

#EBCdotstream #SouthEthiopia #Dasenech #Turkana #Ateker