የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሐሳብ እና ቁጭት ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገረ እንደሆነ ሁሉ ከሥርዓት ወደ ሥርዓትም የተሸጋገረ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
ከንቲባዋ “ኢትዮጵያ ችላለች” በሚል መሪ ቃል በመስቀል አደባባይ በተካሄደው ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የሕዳሴው ግድብ “ሐሳቡም፣ ጅምሩም የመነጨው ከለውጡ በፊት እንደሆነ ታሳቢ አድርገን ካሰቡት እስካስጀመሩት ሁሉ ምስጋና እናቀርብላቸዋለን” ብለዋል።
ሆኖም ግን ልንማርበት የሚገባው ገና የግድቡ ግንባታ ከመጀመሩ ውስን ባንዳዎች እና ባዳዎች በሴራቸው ተባብረው፣ ድምፅ አልባ እንቅፋት አስቀምጠው ግድቡ እንዳይገደብ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰዋል።
የዓባይን ውኃ ‘ብቻችንን ካልተጠቀምን’ የሚሉ የኢትዮጵያ ተቀናቃኞች፣ መጀመሪያ አካባቢ “ኢትዮጵያ አትችልም” ብለው በንቀት የደመደሙት አጀንዳ ሆኖ ስለነበር በወቅቱ ምንም ዓይነት ተቃውሞ እንዳላሰሙም ጠቁመዋል።
ነገር ግን ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገረው ቁጭት እና የሕዝብ አደራ እንቅልፍ የነሣው የለውጡ መንግሥት እና የለውጡ የፊት መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት የሕዳሴ ግድብን በመገምገም ግድቡን ከገባበት ቅርቃር የሚያወጣ ቆራጥ ውሳኔ ወስነው ዳግም ወደ ሥራ በማስገባት ሕይወት እንደዘሩበት ገልጸዋል።
“ያኔ አካሄዱ ያልጣማቸው እና ሴራቸው ሊከሽፍ መሆኑ የገባቸው፣ ‘ብቻችንን ካልተጠቀምን’ ባዮች ከያሉበት ጮኹ፤ ከውስጥ እና ከውጭ ከሰሱን፤ ተባበሩብን፣ ወነጀሉን፣ የዓለም ርዕሰ ጉዳይ አደረጉን። በእጅ አዙር እና በእርስ በርስ ጦርነት እንዲሁም በሚዲያ ዘመቻ የሚችሉትን ሁሉ አዘመቱብን፤ ሊያዳክሙንም ሞከሩ” ሲሉ ዘርዝረዋል።
“ሆኖም፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቆርጠን ስንነሣ የትኛውም ዓይነት ተፅዕኖ እና ጫና ሊያስቆመን አይችልምና በራሳችን ገንዘብ፣ በእኛው ሠራተኞች ላብ እና የደም ዋጋ ጭምር ወደ ፊት ገሰገስን፤ ሕዳሴን ገነባነው፤ ጨረስነው፤ አስመረቅነው!” ብለዋል ከንቲባ አዳነች በንግግራቸው።
“በዚያ ከባድ ፈተና ውስጥ በቆራጥነት፣ ጥበብ በተሞላበት ፅኑ አቋም እና ፅናት ታጥቀው ላስታጠቁን፣ በከፍተኛ ትጋት እንድንገነባ ለመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና አመራራቸው ከልብ ምስጋና እናቀርባለን! ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች፣ አዲስ አበባ ታመሰግናችኋለች!” ሲሉም አመስግነዋል።
በዮናስ በድሉ
#GERD #Ethiopia #ebcdotstream