ሕዳሴ የጎበጠን ሀሳብ ለማቅናት፣ አግድም የሄደና የተዛነፈን አፈጻጸም ለማቅናት የሚተጉ፣ እንዲሁም ስግብግብነትን የሚጠየፉ መሪዎች ሲኖሩ ሥራ እና ሠራተኛ ይስማማል፤ ሥራ ይሰምራል፤ የሥራ ባህልም ይዳብራል የሚል ታላቅ መልዕክት እንዳለው ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ደስታውን ለመግለፅ መስቀል አደባባይ ለወጣው ሕዝብ ባደረጉት ንግግር፥ "በዚህ ታላቅ አደባባይ ላይ ተሰባስበን የሁላችንም የአእምሮ፣ የዕውቀት፣ የላብ፣ የደም፣ የጉልበት እና የሀብት ውጤት የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅ እና በይፋ ወደ ሥራ መግባትን ለመዘከር መገናኘታችን ታላቅ የደስታ እና የፍስሃ ቀን ስለሆነ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ" ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውን አርቀው ያስባሉ፣ ይመራመራሉ፣ ይፈጽማሉ፤ ደግሞም ሠርተው ያሳያሉ፣ ከበረከቱም ያካፍላሉ የሚለውን እሴት እና ትውፊት የሚያሳይ መሆኑንም ነው ፕሬዚዳንቱ ያወሱት።
"የሕዳሴ ግድብ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ሀሳባዊ ኃይሉ ብርቱ ነው፤ እኛ ኢትዮጵያውያን እንችላለን ነው መልዕክቱ፤ ዋና ፍሬ ሀሳቡ እንችላለን፣ ደግመንም እንችላለን ነው፤ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ተመጽዋች፣ ተለቃች የሚለውን መዛበቻ ቅጥያ ስም አሽቀንጥረን ለመጣል ከወሰንን፣ እንችላለን ነው መልዕክቱ" ብለዋል ፕሬዚዳንት ታየ።
አስቸጋሪው እና ሞገደኛው ዓለም ‘እናንተ የድህነት እና ረሃብ ምሳሌዎች ናችሁ’ ሲለን "ይህ ሀሰት፣ እብለት ነው፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ብርቱ ነን፤ መሥራትም እንችላለን የሚል መልዕክት ያስተላለፍንበት ነው" በማለት የግድቡ መጠናቀቅ ያለውን ብርቱ መልዕክት ገልጸዋል።
ግድቡ እንደ ብርቱ ቋሚ እና ማገር፣ እንደ ጠንካራ ድር እና ማግ ከተቀናጀ፤ ዒላማውን እና ግቡን ከለየ፤ ኢትዮጵያዊው ይችላል፤ ከቶ የሚሳነው የለም የሚል መልዕክትም እንዳለውም ፕሬዚዳንቱ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
"የሥራን ታላቅነት እና አሸናፊነት ፍንትው አድርጎ ማሳየቱም ሌላው መልዕክቱ ነው" ያሉት ፕሬዚዳንት ታየ፣ የሚያስቡ አእምሮዎች፣ ለተግባር የተጉ የጥበብ እጆች፣ ለመጀመርም ሆነ በወጉ ለመጨረስ የተጉ መሪዎች እና ሠራተኞች ሲኖሩ፤ ዕድገት፣ ሀሳብ እና መልካም ተግባር ተስማሙ፣ ተዋሀዱ ማለት መሆኑን ገልጸዋል።
ኃይል ማመንጨት እና በአግባቡ ማድረስ የፍትሕ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የዕድገት መሰላል እንደሆነ ጠቅሰው፤ በቂ የኃይል አቅርቦት ከሌለ ከትንሿ አገልግሎት ጀምሮ እስከ ታላላቅ ኢንዱስትሪዎች መሥራት፣ ማምረት እና የንግድ አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል።
"ማደግ እና በእጅጉ መዘመንን ዋና መንገዳችን አድርገን ስለወሰድን፣ የኃይል ምንጭን እናሳድጋለን፤ ይህን በዓይነትም፣ በብዛትም ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ተምረናል" በማለት ሕዳሴ ለኢትዮጵያ ዕድገት ያለውን ድርሻ አውስተዋል።
በለሚ ታደሰ
#EBCdotstream #GERD #taye_atske