በምድር ላይ በጣም ቀላል “ሞለኪውል” የሆነው ሃይድሮጅን በአብዛኛው ለማጣሪያ እና ለኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ኃይል በማመንጨት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡
እስካሁን ያለው ሃይድሮጅን ጋዝ የሚገኘው ታዲያ ከፍተኛ ካርቦን በማመንጨት አካባቢን ከሚበክሉት የሚቴን ጋዝ እና ከድንጋይ ከሰል ነው።
ይሁን እንጂ አነስተኛ ካርቦን ያለውን እና ለአካባቢ ብክለት ስጋት የማይፈጥር ሃይድሮጂን ለማመንጨት የሚያስችሉ ሌሎች መንገዶችም እንዳሉ ተመራማሪዎች እየጠቆሙ ነው።
እንደ ተመራማሪዎቹ መረጃ ነጭ ወርቅ የሚባለው አዲሱ ሃይድሮጂን ከነዳጅ በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ኃይል ለማመንጨት ከመቻሉም በላይ ከተቃጠለ በኋላ ውኃ ብቻ የሚያመነጭ ንጹህ የኃይል ምንጭ ነው፡፡
እንደ አውሮፕላን፣ መርከብ እንዲሁም የብረት ፈብሪካዎች ላሉ ኢንዱስትሪዎች ንጹሕ የኃይል አማራጭ እንደሆነም እየተነገረለት ነው።
ከዚህ ሃይድሮጂን የሚገኘው አረንጓዴ የኃይል ምንጭ ከዘይት ነዳጅ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ካርቦን የሚያመነጭ መሆኑም ሌላው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩረት የሳበ ጉዳይ ነው።
የሃይድሮጂን ጋዝን የመጠቀም ልማድ ቀስ በቀስ እያደገ ቢሆንም ከዓለም የሃይድሮጂን ምርት ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው ግን 1 በመቶ የሚሆነው ብቻ መሆኑ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ነው ተመራማሪዎች የሚጠቁሙት።
በተፈጥሮ የሚገኘው እና ከብክለት ነጻ የሆነው የዚህ ሃይድሮጅን ክምችት ቀደም ሲል ከታሰበው በላይ በጣም ብዙ እንደሆነ ተደርሶበታል፡፡
ይህ "ጂኦሎጂክ" ሃይድሮጅን ወይም ተፈጥሯዊ ነጭ ሃይድሮጅን ተብሎ የሚታወቀው ጋዝ የሚገኘው በብረት የበለጸጉ ዓለቶች ውስጥ ነው።
ተመራማሪዎች በቀጣይ ለንጹህ የኃይል ምንጭ ተስፋ የጣሉበት ይህን በምድር ወለል ውስጥ የሚገኘውን የሃይድሮጂን ክምችት ነው።
የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ (USGS) በ2024 ባደረገው ጥናት መሠረት ከ1 ቢሊዮን እስከ 10 ትሪሊዮን ቶን ሃይዲሮጂን በከርሰ ምድር እንደሚገኝ እና ከዚህ ውስጥም 5.6 ትሪሊዮን ቶን ገደማ የሚሆነው በአስቸጋሪ የመሬት አቀማመጥ ምክንያት ተደብቆ እንደሚሆን ጠቁሟል።
የጥናቱ አዘጋጆች የሆኑት ጄፍሪ ኤሊስ እና ሣራ ጌልማን እንደገለጹት አብዛኛው የሃይድሮጂን ክምችት መገኛ በጣም ጥልቀት ባለው ከርሰ ምደር፣ በባሕር ዳርቻ፣ በጣም ሩቅ በሆነ ወይም ሊደረስበት በማይችል አካባቢ ውስጥ ሊሆን ይችላል።
ይሁን እንጂ ከዚህ ነጭ ሃይድሮጅን ውስጥ 2 በመቶውን ብቻ መጠቀም ቢቻል ለ200 ዓመታት ያህል የዓለምን የኃይል ፍላጎት ማሟላት እንደሚችል በጥናታቸው ደርሰውበታል።
በተጨማሪም ነጭ ሃይድሮጂን በኃይል ምንጭነት ከሚታወቁት የተፈጥሮ ጋዞች በሙሉ በእጥፍ የሚበልጥ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው አክለዋል።
ይህ ሐሳብ ምድር በከርሷ ምን ይዛለች ለሚለው ጥያቄ አሁንም ገና ብዙ ሊሠራ እንደሚገባ የጠቆመ መሆኑን እና ለምርምር ከፍተኛ መነሳሳትን እንደፈጠረ ይነገራል።
በአሁኑ ወቅት ቢያንስ 60 ኩባንያዎች ነጭ ሃይድሮጂንን ለማግኘት ፍለጋ እያደረጉ እንደሆነ ተገልጿል።
ኢንቨስትመንቱም 1 ቢልዮን ዶላር ደርሷል ተብሎ እንደሚገመት የዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ (IEA) የነጭ የሃይድሮጂን ኤክስፐርት ቡድን መሪ የሆነው ፈረንሳዊው የጂኦኬሚስትሪ ባለሙያ ኤሪክ ጎቸር ይናገራል።
በሚቀጥሉት ሦስት ወይም አራት ዓመታት ውስጥ በዚህ ረገድ ትልቅ እምርታ ሊኖር እንደሚችል እና ተፈጥሯዊው ሃይድሮጂን ነዳጅ ከዚህ ቀደም የነበረውን ሚና ሊተካ እንደሚችል ጎቸር ተስፋ አድርጓል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይ በሚገኙ የፒረኒ ተራሮች ላይ ነጭ ሃይድሮጅን ለመፈለግ የሚንቀሳቀሰው ‘ማንትል 8’ የተባለው ኩባንያ በየካቲት 2025 የገንዘብ ድጋፍ አግኝቷል።
ኩባንያው በ2028 የዳሰሳ ቁፋሮ ለመጀመር እና በ2030 አንድ ኪሎ ግራም ሃይድሮጅን በ0.80 ዶላር ገደማ ለማምረት ዕቅድ ይዟል።
ይህም ከየትኛውም የኃይል ምንጭ ከሆኑት ጋዞች በአምስት እጥፍ ርካሽ እና አረንጓዴ የኃይል ምንጭን ለማግኘት ይረዳል ተብሏል።
የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎችም ነጭ ሃይድሮጂን 1 ኪሎ ግራም ከ0.74 የአሜሪካ ዶላር በታች በሆነ ዋጋ ሊመረት እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በአሁኑ ወቅት በአንድ በኩል ከፍተኛ የኃይል ምንጭ፣ በዚያው መጠን ደግሞ ከኢንዱስትሪዎች የሚጣው ካርቦን አካባቢን እየበከለ ዓለምን ስጋት ውስጥ አስገብቷል፡፡
በዚህ ዓለም አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ወቅት በትንሽ ወጪ ዝቅተኛ ብክለት ያለው የኃይል ምንጭ ለማግኘት እየተደረገ ባለው ጥረት የነጭ ሃይድሮጅን መገኘት ትልቅ ተስፋ መሆኑን ተመራማሪዎች እየገለጹ ነው፡፡
በለሚ ታደሰ