Search

"አዲስ አበባን የመረዳዳትና የመተሳሰብ ተምሳሌት እናደርጋለን" - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ረቡዕ የካቲት 25, 2018 41

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ዛሬ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ሙስሊም እህትና ወንድሞቻችን ጋር የአብሮነት መገለጫ በሆነችው በውቧ አራዳ ፓርክ የኢፍጣር መርሐ-ግብር አካሂደናል ብለዋል።

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ መርሃ ግብሩ የከተማዋን የአብሮነትና የመተሳሰብ እሴት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የሙስሊሙ ማኅበረሰብ በታላቁ የረመዳን ጾም፣ የክርስትና እምነት ተከታዮች ደግሞ በታላቁ ዓቢይ ጾም ላይ መሆናቸውን የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ ይህ ወቅት ያለ ሃይማኖት ልዩነት እርስ በእርስ የምንጠያየቅበትና "ምን ጎደለ?" የምንባባልበት ልዩ ጊዜ ነው ብለዋል።

በዚህም ምክንያት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ወገኖች ጋር የሚደረገው የኢፍጣር መርሃ ግብር በሁሉም የከተማዋ ክፍለ ከተሞች በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከተማዋን የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ተምሳሌት የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ መልዕክታቸው አረጋግጠዋል።

#EBC #Ethiopia #AddisAbaba #AdanechAbiebie #Iftar2026 #Ramadan #AradaPark