“እንኳን ደስ ያለን!” በማለት የመልካም ምኞት መግለጫቸውን ያስቀደሙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድርን በአዲስ አበባ ለማዘጋጀት ታሪካዊ ዕድል ማግኘቷን አብስረዋል።
ከንቲባዋ ይህ ድል በከተማዋ ሲከናወን የቆየው የዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ የስፖርት ዲፕሎማሲ እና የመሠረተ ልማት መስፋፋት ሥራ ፍሬ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ በዓለም አትሌቲክስ ካላንደር ውስጥ በይፋ የተካተተውና "One Day Meeting" የተሰኘው ውድድር፣ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ሚያዝያ 18 ቀን 2026 በአዲስ አበባ የሚከናወን ይሆናል።
ስኬቱ የተመዘገበው የዓለም አትሌቲክስ የውድድር ዋና ዳይሬክተር ፒርስ ኦክላጋን በኢትዮጵያ ያደረጉትን የሥራ ጉብኝትና አገሪቱ ያላትን በቂ የማዘጋጀት አቅም መመስከራቸውን ተከትሎ ነው።
ውድድሩ በዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የሚመራ በመሆኑ ለአገር ውስጥ ሙያተኞች ትልቅ የልምድ ልውውጥ የሚፈጥር ሲሆን፣ ከተለያዩ አገራት ለሚሳተፉ አትሌቶችም ከፍተኛ ሽልማት ያበረክታል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለዚህ ውጤት መመዝገብ የላቀ ሚና ለተጫወቱት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ዕውቅናና ምስጋና ሰጥተዋል።
ይህ አዲስ ምዕራፍ ኢትዮጵያ የአትሌቲክስ መገኛነቷን በላቀ ደረጃ ለዓለም የምታሳይበትና የስፖርት ዲፕሎማሲዋን ወደ ከፍታ የምታደርስበት መድረክ እንደሚሆንም ታምኖበታል።
#Ethiopia #WorldAthletics #SportsDiplomacy #AdanechAbiebie #AthleticsEthiopia #EthiopianBroadcastingCorporation