Search

"በእነዚህ ሕዝቦች ተደንቄአለው" :- ሕዳሴን አጠናቅቀው ኮይሻን እያገባደዱ ያሉት ኢትዮጵያውያን

እሑድ መስከረም 18, 2018 96

በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች አፍሪካን የተመለከቱ መረጃዎችን የሚያጋራው አርኬአይቪ ፕሮ አፍሪካ፤ ኢትዮጵያውያን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ አጠናቅቀው የኮይሻን ግድብን እያገባደዱ ያሉ ጠንካራ መሪ ያላቸው ድንቅ ሕዝቦች ናቸው ይላል።
ኢትዮጵያዊያን ለአፍሪካውያን ምሳሌ መሆናቸውን ቀጥለዋል ሲልም የገለፀው ዘገባው፤ ይህም ተስፈኛ እና ጠንካራ መሪ እንደአላት ያሳያል ሲል ጠቅሷል፡፡
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ኢትዮጵያውያን የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ባስመረቁ ማግስት የኮይሻ (ጊቤ 4) ግድብን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉም ሲል ዘገባው ያነሳል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁ የኃይል ማመንጫ ግድብ ቢኖራትም የኃይል አቅርቦት ፍላጎቷን ለማሳካት ተጨማሪ ኃይል ማቅረብ የሚችል የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታ ስምምነትን ከሩሲያ ጋር መፈራረሟንም ጠቅሷል ፡፡
"በእነዚህ ሕዝቦች ተደንቄአለው" የሚለው ዘጋቢው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ልማቶችን በሀገሪቱ ላይ በመስራት ተዓምራዊ ለውጥ እያመጣ ስለመሆኑም ነው የገለጸው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ለሀገሪቱ ጥቅም ላይ የሚውል እንደሆነ እና ይህም ለሀገሪቱ እድገት ያለውን ጥልቅ ራዕይ የሚገልጽ ስለመሆኑ ነው የጠቀሰው፡፡
ይህ ለአፍሪካ መሪዎች መማሪያ ሊሆን ይገባል ሲልም አንስቷል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ከመሪያቸው ጋር እያስመዘገቡት ላለው ስኬት "እንኳን ደስ ያላችሁ" ከማለት ውጪ ሌላ ምርጫ የለንም ሲልም ዘገባው ሃሳቡን ቋጭቷል።
 
በሜሮን ንብረት