የቀድሞውን የመንግሥታቱን ማኅበር የተካው የመንግሥታቱ ድርጅት እነሆ 80 ዓመታትን ደፍኗል፡፡
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅን ተከትሎ የተመሰረተው ተመድ ዓለምን ወደ ትብብር መድረክ ያመጣል ተብሎ ቢታሰብም የቆመለትን ዓላማ ሳያሳካ የአንድ አረጋዊ ዕድሜን እንደጨረሰ ነው በርካቶች የሚያምኑት፡፡
ዋና ዓላማው ሁሉን አቀፍ የዓለም ሥርዓት ማጠናከር ቢሆንም ዓለምን ፈተና ውስጥ ያስገቡ የተናጠል እርምጃዎችን ማስቆም አልቻለም ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡
አፍሪካ ደግሞ በተናጠል እርምጃዎች የተጎዳች ሀገር መሆኗን አሁን ያለችበት ምስቅልቅል ማሳያ እንደሆነም ያነሳሉ፡፡
አፍሪካ ድርጅቱ በቻርተሩ ላይ የተጠቀሱትን የአካታችነት መርሆችን ተግባራዊ በማድረግ ይህን አለመመጣጠን ለማስተካከል ተሐድሶ እንዲያደርግ መጠየቅ ከጀመረች ውላ አድራለች፡፡
አህጉሪቱ በፀጥታው ምክር ቤት እና በዓለም አቀፍ የፋይናስ ተቋማት የሚገባትን ውክልና እና ድምጽ እየጠየቀች ቢሆንም አስካሁን ግን በድርጅቱ በኩል ያለው ምላሽ የሚያወላዳ አይደለም፡፡
በ80ኛው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤም አፍሪካ ታሪካዊ ድምጿን ማሰማቷን ቀጥላለች፡፡ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴን ጨምሮ ሁሉም የአፍሪካ መሪዎች እነዚህን ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡
ለመሆኑ አፍሪካ የጠየቃቻቸው ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
የፀጥታው ምክር ቤት (UNSC) ማሻሻያ
የአፍሪካ መሪዎች አሁን ያለው የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት መዋቅር ኢፍትሃዊ እና ትክክለኛ ውክልና የሌለው እንደሆነ ጠቅሰዋል።
1.4 ቢሊዮን ሕዝብ ያላት አፍሪካ በምክር ቤቱ ውስጥ የበይ ተመልካች ሆና መኖር እንደሌለባት መሪዎቹ አጽንኦት ሰጥተው ጠይቀዋል፡፡
የኢስትዋኒ ስምምነት አፍሪካ ሁለት ቋሚ መቀመጫዎች እና ሁለት ተለዋዋጭ መቀመጫዎች እንዲኖራት ይጠይቃል።
ድርጅቱ የበለጠ ውጤታማ እና ሕጋዊ እንዲሆን አፍሪካ በዚህ ጉዳይ ላይ "አስቸኳይ" ምላሽ መስጠት እንዳለበትም መሪዎቹ አሳስበዋል።
የዓለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ማሻሻያ
ሌላው በአፍሪካ መሪዎች ልዩ ትኩረት የተሰጠው የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ተቋማት ሥርዓት ነው፡፡ አሁን ያለው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአፍሪካን የልማት ፕሮጀክቶች ከማበረታታት ይልቅ እንደሚያዳክሙ መሪዎቹ በአጽንኦት ተናግረዋል።
መሪዎቹ በትኩረት የጠቀየቁት በአፍሪካ ላይ የተጫነው ዕዳ ስረዛ፣ የተቋማቱ ሪፎርም እና አካታችነት እርምጃን የተመለከተ ነው።
አፍሪካ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና በዓለም ባንክ አስተዳደር ውስጥ ውክልናዋ እንዲጨምር እና ለአፍሪካ በሚሰጡ ብድሮች ላይ ያለው የተዛባ የወለድ ምጣኔ እንዲስተካከል መሪዎቹ ጠይቀዋል።
የአየር ንብረት ፍትህ እና ፋይናንስ
አፍሪካ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ የምታበረክተው አስተዋጽኦ አነስተኛ ቢሆንም፣ እንደ ድርቅ እና ረሃብ ባሉ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚከሰቱ ችግሮች እየተሰቃየች ትገኛለች።
በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት አፍሪካ ይህን ችግር እንድትቋቋም የ100 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ የአየር ንብረት ፋይናንስ ቃል ተገብቷል፡፡
ይህ ገንዘብ የአህጉሪቱን የማላመድ እና የችግሩን ተፅዕኖ የመቀነስ ጥረቶችን ለመደገፍ እና በካርቦን ልቀት ምክንያት የደረሰባትን ኪሳራ እና ጉዳት ለማካካስ የሚውል ፈንድ ነው። መረዎቹ ዓለም ይህን ቃሉን እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሰላም፣ ደኅንነት እና ሉዓላዊነት
በአፍሪካ ውስጥ ለሚከሰቱ ግጭቶች አፍሪካውያን የመፍትሔዎች አቅጣጨዎቹን ራሳቸው መምራት እንዳለባቸው የጠየቁት መሪዎቹ፣ የውጭ ወታደራዊ ጣልቃገብነት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
መሪዎቹ በሱዳን እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያሉ ግጭቶችን ውስጥ ያለውን የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትን አውግዘው፣ ለየትኛውም በአፍሪካ ውስጥ ለሚከሰት የሁለት ሀገራት እና የውስጥ ግጭቶች አፍሪካ የራሷን መፍትሔ እንድትሰጥ ጠይቀዋል።
አፍሪካ ለዕድገቷ ወሳኝ የሆኑ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ምክንያት የግጭት መንስኤ በሆኑ ማዕድኖቿ ላይ ራሷ እንድትወስን (የማዕድን ሉዓላዊነት ዕውቅና እንዲኖራት) ጠይቀዋል።
"በሁሉም ቦታ የተኩስ ድምጽ እንዳይኖር" በተመድ እና እንደ አፍሪካ ኅብረት ባሉ የአህጉሪቱ ተቋማት መካከል መናበብ እንዲኖርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሁለቱ መናበብ የሚመራውን የሰላም ማስከበር ዘመቻ ለማጠናከር እና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ተመድ ለእውነተኛው ትብብር ራሱን እንዲያዘጋጅ ጠይቀዋል።
በለሚ ታደሰ
#EBC #ebcdotstream #Africa #UNassembly #UNSC