Search

‎"ቻሎ" - የየም ብሔረሰብ ባህላዊ ዳኝነት

እሑድ መስከረም 18, 2018 87

በአካባቢው ቦር ተብሎ በሚጠራው ተራራ አናት ላይ በሚገኘው ሰፊ እና አረንጓዴ ሜዳ ላይ የየም ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል 'ሄቦ' በድምቀት ይከበራል።

ታዲያ ቦር ተራራ በዓል ማክበሪያ ብቻ ሳይሆን ባህላዊ ዳኝነት መከወኛም ነው። የዳኝነት ስርዓቱም 'ቻሎ' ይሰኛል።

በዓሉ በተለያዩ ትዕይንቶች የሚከበር ሲሆን ከበዓሉ ጎን ለጎን ውሳኔ የሚሰጡ ዳኞች በስፍራው ይሰየማሉ።

ጉዳያቸው እንዲታይላቸው የሚፈልጉ ግለሰቦች ሰልፍ በመያዝ በየተራ የደረሰባቸውን በደል ለዳኞች ያስረዳሉ።

ጉዳዩን እንዲያስረዳ ዕድል የተሰጠው ሰው ከዳኞቹ ፊት በመንበርከክ ደረሰብኝ ስለሚለው በደል ያብራራል።

በዚህ ባህላዊ ችሎት በአብዛኛው የሚቀርቡ አቤቱታዎችና ክሶች የቤተሰብ የርስበርስ አለመግባባት፣ ግጭት እና በአካባቢው በግለሰቦች መካከል የተፈጠረ መካካድን (ምሳሌ:-ገንዘብ ተበድሮ ማስቀረት) የመሳሰሉ ጉዳዮች ተከሳሽ በተገኘበት በዳኞች ይታያሉ።

ዳኞች ሁለቱንም ወገኖች በማድመጥና በማከራከር ዕውነታው ማን ጋር እንደሆነ ይገነዘባሉ።

በየም ብሔረሰብ ዘንድ በዚህ ባህላዊ ዳኝነት ላይ ከፍተኛ ዕምነት በመኖሩ እና ዋሽቶ የተከራከረ ሰው ላይ አንዳች ያልታሰበ አደጋ ይደርስበታል ተብሎ ስለሚታመን በዳይና ተበዳይ ሀቁን ለዳኞች ይናገራሉ።

ባህላዊ ዳኞችም ግራ ቀኙን አይተው ካመዛዘኑ በኋላ ፍርድ ይሰጣሉ።

የሚቀጥለው ዘመን መለወጫ 'ሄቦ' ከመከበሩ አስቀድሞም ተከሳሽ የተላለፈበትን ፍርድ እንዲፈፅም ይጠበቃል።

ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ከውሳኔው አንድ ዓመት በኋላ የሚሰየመው ዳኛ በህዝብ ፊት ግለሰቡ ከማህበረሰቡ እንዲገለል ውሳኔ ያሳልፋል።

የዘንድሮው የየም ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ 'ሄቦ' በዓል የፊታችን መስከረም 21 እና 22 በደማቅ ስነ-ስርዓት በየም ዞን ይከበራል፡፡

በሲሳይ ደበበ

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #የም #ቻሎ