ለበርካታ ዓመታት ነፍጥ አንግበው ህዝብን ሰላም ሲነሱ እና ልማት ሲያደናቅፉ የነበሩ የሸኔ ታጣቂዎች መንግሥት የሚያቀርበውን ያልተቋረጠ የሰላም አማራጭ በመቀበል የቡድኑ አመራር ጃል በርሲሳን ጨምሮ 73 አባላት፥ 7 ብሬን፣ 4 ስናይፐር፣ 50 ክላሽ እና ሌሎች ኋላቀር መሳሪያዎችን ይዘው እጃቸውን ሰጥተዋል።
ወዶ ገቦቹ የሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን መቀመጫ ወደሆነችው ሻምቡ ከተማ የገቡ ሲሆን፤ የቴዎድሮስ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄነራል ረሺድ ኢብራሂምን ጨምሮ የክፍለጦር አመራሮች የወረዳ አመራሮች፣ አባገዳዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በዚህ በሰለጠነ ዘመን ዓላማ የሌለው ትጥቅ አንግቦ በጫካ መኖር ትርፉ ውድቀትና ኪሳራ ነው ያሉት ብርጋዲየር ጄነራል ረሺድ ኢብራሂም፤ የሰላምን ምንነትና አስፈላጊነት ተረድተው እጅ ለሰጡ የሸኔ አባላት በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር ወደ ህብረተሰቡ ተመልሰው መሥራት እንዲችሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን ብለዋል።
ኮሩ በየተሰማራበት የግዳጅ ቀጠና እጥፍ ድርብ ድል እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የሰላም አማራጭን ወደ ጎን በመተው በየጫካው የሚሽሎከለኩ የቡድኑ አባላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የኮሩ ዘመቻ ሃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ጌታነህ አሰፋ በበኩላቸው፥ ኮሩ በቀጠናው ሌት ተቀን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በሚያደርገው አሰሳና ስምሪት በርካታ ድሎችን እያስመዘገበ መሆኑን አንስተው፤ ይህም አንዱ የስምሪታችን አቅም ማሳያ ውጤት ነው ብለዋል።
አክለውም፥ ይህ ትልቅ ስኬት የሠራዊቱን ሞራል እና የማድረግ አቅም ከፍ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
#EBCdotstream #Ethiopia #ENDF