Search

የቱሪዝም ዘርፉን የሚያነቃቃው የመስከረም ወር

ሰኞ መስከረም 19, 2018 31

ወርሃ መስከረም የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ በርካታ ባህላዊ እና ሐይማኖታዊ በዓላት ይስተናገዱበታል።
ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም ደግሞ የግልም ሆነ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ይበልጥ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ይነሳል።
በኢትዮጵያ ቱሪዝም እና ሆቴል ገበያ ማኅበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ አስማ መፍቱ ፤ “የመስከረም ወር የቱሪዝም ዘርፉን ማነቃቃት የሚያስችል ወርቅ የሆነ ዕድልን ይዞ መጥቷል” ይላሉ።
መስከረም የተለያዩ የአደባባይ በዓላት የሚከበሩበት ወር እንደመሆኑ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ቱሪስቶች የሚገኘውን ገቢ ከፍ ለማድረግ የተቀናጀ ሥራ ማከናወን እንደሚያስፈልግም ነው ያመላከቱት።
የአደባባይ በዓላቱን ተከትሎ የሚመጡ ቱሪስቶችን በተሻለ የአገልግሎት ጥራት ማስተናገድ እንደሚገባም አንስተዋል።
በኦሮሚያ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ቡድን መሪ አቶ ደረጄ ጀቤሳ በበኩላቸው ፤ በመስከረም ወር የሚከበሩ ባህላዊ እና ሐይማኖታዊ በዓላት ቱሪስቶችን የመሳብ አቅም እንዳላቸው ነው የጠቆሙት።
በቀጣይም በርካታ ቱሪስቶች በኢሬቻ በዓል ላይ ለመታደም እንደሚመጡ አንስተው፤ የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘምም አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዓባይ መንግሥቴ ፤ የመስከረም ወር የተለያዩ የአደባባይ በዓላት የሚስተናገዱበት እንደመሆኑ የቱሪዝም ገቢን ለማሳደግ ምቹ ወቅት ነው ይላሉ።
ወደክልሉ የሚመጡ ቱሪስቶችን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ እና የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘምም እየተሰራ መሆኑን ነው የገለፁት።
 
በሜሮን ንብረት