Search

ፍርድ ቤቶች የሰላም፣ የመረጋጋት እና እንደ ሀገር ፀንቶ የመቆም ምሶሶዎች ናቸው - አቶ ዓለምአንተ አግደው

ማክሰኞ መስከረም 20, 2018 179

የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኞች ጉባኤ በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው፦ ፍርድ ቤቶች የሰላም፣ የመረጋጋት እና እንደ ሀገር ፀንቶ የመቆም ምሶሶዎች ናቸው ብለዋል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቶች ፍትሕን በማስፈን ውጤታማ ማህበራዊ ግንኙነትን ለመፍጠር፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንዲሁም ልማትን ለማፋጣን ሚናቸው ትልቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ፍርድ ቤቶች እና የፍትሕ አካላት ነፃ እና ገለልተኛ ሆነው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። በክልሉ ከዚህ አንፃር የሚታዩ ችግሮችን የማረም እና የማስተካከል ሥራ እየተከናወነ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት።

በክልሉ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን እና የተሻሉ ዳኞች ማፍራትን ጨምሮ የፍርድ ቤቶችን  የህዝብ ቅቡልነት እና ተዓማኒነት ለማሻሻል ስር ነቀል የለውጥ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በቀጣይም የፍርድ ቤቶችን ተግዳሮቶች በመፍታት እንዲሁም ለባህላዊ ፍርድ ቤቶች እውቅና በመስጠት የፍትሕ አሰጣጡን እንዲያግዙ ለማድረግ ይሠራል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው፥ ፍርድ ቤቶች ፍትሕን በማስፈን በህዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የፍርድ ቤቶች እና የፍትሕ አካላትን አሠራር የማስተካከል፣ አዋጅና ፖሊሲዎችን የማሻሻል እና ሌሎችም ሥራዎች በክልሉ በትኩረት  እየተከናወኑ ስለመሆናቸው አብራርተዋል።

ጉባኤው በ10 ቀናት ቆይታው የክልሉ የዳኝነት ዘርፍ ጉዳዮችን ይዳስሳል ተብሎ ይጠበቃል።

በጉባኤው ከክልሉ ከሁሉም አካባቢዎች የተውጣጡ ከ2 ሺህ 200 በላይ ዳኞች እንዲሁም የጉባኤ ተሿሚዎች እየተሳተፉ ነው።

በሳሙኤል ወርቃየሁ

#EBCdotstream #Amhara #Courts #Judges